
ባሕር ዳር: ኅዳር 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ለስደት ተመላሾች ማቋቋሚያ የሚሆን የ1 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።
ድጋፉ ለስደት ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ለሚደረገው የሰብአዊና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሁም ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከሳውዲ አረቢያ የሚመለሱ 18ሺ 100 ዜጎችን ለመቀበል፣ በመጠለያ ለሚያርፉ ተመላሾች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አገልግሎቶችን ለመስጠት እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚያስችሉ የኅብረተሰብ ንቅናቄና ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚውልም ተገልጿል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የሳውዲ አረቢያን መንግሥት ላደረገው ድጋፍ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
የተደረገው ድጋፍ ለስደት ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ለሚደረገው የሰብአዊና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሁም ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር ፉሃድ ኦባይዱላህ የሳኡዲ አረቢያ መንግሥት ወደፊትም ድጋፍ ማድረጉን የሚቀጥልና በትብብር የሚሠራ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
ፕሮጀክቱን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን እና የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በመተባበር ተግባራዊ የሚያደርጉት ይኾናል።
የገንዘብ ድጋፍ ፕሮጀክቱ የንጉስ ሳልማን የሰብአዊ ድጋፍና እርዳታ ማዕከል በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) በኩል ተደራሽ የሚኾንና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ መኾኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!