
ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ማደበሪያ አቅርቦትን በተመለከተ በየደረጃው ከሚገኙ መሪዎች ጋር ተወያይቷል።
ውይይቱ በአፈር ማደበሪያ አቅርቦት የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ በወቅቱ ማቅረብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነው።
ውይይቱን የመሩት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር) በባለፈው ዓመት የተፈጠረውን ችግር እንደ ትምህርት በመውሰድ ለዘንድሮ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
ለተፈጠረው ችግርም አርሶ አደሮችን ይቅርታ ጠይቀናል፤ ድጋሜ እንዳይፈጠርም አበክረን እየሠራን ነው ብለዋል።
የግብርና ሥራ በመተቻቸት ሳይኾን ኀላፊነትን በመወጣት የሚሠራ መኾኑንም ገልፀዋል። የአርሶ አደሮች አገልጋዮች ነን ብለን ማመን አለብንም ብለዋል።
በፌዴራል መንግሥት በኩል ፍትሃዊ የማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙንም ተናግረዋል። ማዳበሪያው ከበፊቱ አስቀድሞ መግባት መጀመሩንም ገልጸዋል። እንደ ክልል የሚጠበቅብንን መወጣት ይገባናልም ብለዋል። የግብዓት አቅርቦትን በጥናት በመደገፍ መጠየቅ እና ማቅረብ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የተገዛውን ግብዓት ሁሉ በአግባቡ ማሰራጨት ከተቻለ ትልቅ ስኬት መኾኑንም ገልፀዋል። በምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣም ተናግረዋል። በግምት የሚመራ የግብርና ዘርፍ አይኖረንም፤ ሁሉም ሙያዊ በኾነ መንገድ ይመራል ነው ያሉት።
የአቅርቦት ችግር ብቻ ሳይኾን የሥርጭትም ችግር በመኖሩ አርሶ አደሮች መማረራቸውን ተናግረዋል። በጊዜ የለንም መንፈስ መሥራት ይገባናልም ብለዋል። የዩኔኔኖች ወደ መጋዘን ማስገባት ዝግጅታቸውን መጨረስ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። ያለባቸውን ችግር እንዲቀርፉም አሳስበዋቸዋል።
የሕግ ተጠየቂነት እንደሚኖርም ተናግረዋል። ከአርሶ አደሮች ጋር በመኾን በሕገ ወጥ መንገድ የሸጡ አካላት ላይ እርምጃ እንወስዳለን ነው ያሉት። በሌሎች አካላት እያመካኙ በሚሸጡ አካላት ላይም እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።
በማልማት ስም የግብዓት አቅርቦት ላይ ችግር በሚፈጥሩ ባለሃብቶች ላይም እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።
“የግብርና ሥራውን የሚያደናቅፍ ሁሉ ፀረ-አማራ ነው፤ የአማራን ሕዝብ በርሃብ ለመቅጣት የሚደረጉ አካሄዶች መታረም አለባቸውም” ብለዋል። አርሶ አደር እንዳይዘራ፣ እንዳይሰበስብ፣ በምጣኔ ሃብት እንዲጎሰቁል የሚያደርግ ሁሉ የአማራ ጠላት ነው፤ ከዚህ በላይ አማራ ጠላት የለውም ነው ያሉት። የክልሉ ሕዝብ በምጣኔ ሃብት እንዳይጎዳ በቅንጅት እና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ምርት ማምረት የሕልውና ጉዳይ ነው፤ ግብርና ከምርትም በላይ ሕልውና ነው፤ የምንታገለው ለሕልውና መኾን አለበት ብለዋል። ግብርናው ከፍ እንዲል በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። አርሶ አደሮች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች መፍታት ይገባናልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!