በ13ኛው የዩኔስኮ የወጣቶች ፎረም ላይ ኢትዮጵያ እየተሳተፈች ነው።

53

ባሕር ዳር: ኅዳር 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) በ13ኛው የተመድ የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ወጣቶች ፎረም ላይ እየተሳተፉ ነው።

ፎረሙ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የወጣቱ ሚና ላይ በትኩረት እየመከረ መኾኑን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ የወጣቶችን ፖሊሲ ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች መኾኑን ጠቁመው፥ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ለወጣቱ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ እንዲሁም አስከፊ ስደትን ለማስቀረት ከሀገራት ጥረት በተጨማሪ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና ተቋማት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመከላከል በአረንጓዴ አሻራ መረሐ ግብር ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ ሰፊ ሥራ መሠራቱንም አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ሚኒስትሯ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከሞሮኮ ወጣቶች ባሕልና ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር መሂድ ቤንሰይድ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል በወጣቶች ዙሪያ የሚሠሩ ሥራዎችን በትብብር መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው የፓን አፍሪካ ወጣቶች ፎረም ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሱዳን ሪፐብሊክ ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጀኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን አዲስ አበባ ገቡ።
Next article“የአማራን ሕዝብ በርሃብ ለመቅጣት የሚደረጉ አካሄዶች መታረም አለባቸው” ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር)