
ባሕር ዳር: ኅዳር 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰው ሠራሽ የአፈር ማደበሪያ አቅርቦትን በተመለከተ በየደረጃው ከሚገኙ የግብርና መሪዎች ጋር ተወያይቷል።
ውይይቱ በሰው ሠራሽ የአፈር ማደበሪያ አቅርቦት ላይ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ በወቅቱ ማቅረብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር ነው።
በውይይቱ የተገኙ የግብርና ቤተሰቦች እና የዩኔን የሥራ ኀላፊዎች በግብርና አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ስርቆቶችን ቁጥጥር ማድረግ ይገባል ብለዋል። በአቅርቦቱ ላይ የነበረው ስርቆት እና ሕገ ወጥ ዝውውር ችግር ፈጥሯል ነው ያሉት።
በግብርና ግብዓት አቅርቦት እና ሥርጭት ላይ ተጠያቂነት ማስፈን እንደሚገባም ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት በአፈር ማደበሪያ ላይ ስርቆት እና ዝርፊያ መፈፀሙንም ተናግረዋል።
በሥርጭት ወቅት የሚፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ሕግ እና ሥርዓትን የጠበቀ ክትትል ያስፈልጋልም ብለዋል። አንዳንድ ባለሃብቶች አለማለሁ በማለት ማዳበሪያ እየወሰዱ በሕገ ወጥ መንገድ እንደሚሸጡም አንስተዋል። በልማት ስም በሚነግዱ ባለሃብቶች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እና እርምጃ መውሰድ ይገባል ነው ያሉት።
ማዳበሪያው በተሳካ መንገድ ወደ አርሶ አደሮች እንዲደርስ ሁሉም ኀላፊነቱን መወጣት ይገባዋል ብለዋል። ሰላሙን መጠበቅ እና የግብርና አቅርቦቱን ተደራሽ ማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
ከባለፈው ችግር ትምህርት በመውሰድ ችግሩን ለመቅረፍ ኀላፊነት መውሰድ ይገባልም ብለዋል። የግብዓት አቅርቦት ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በመውሰድ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ባለፈው ዓመት የነበረው ችግር የፖለቲካ አጀንዳ በመኾኑ በክልሉ የሰላም እጦት እንደ አንድ ምክንያት መኾኑንም አንስተዋል።
የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ባለሙያዎች እና መሪዎች ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ችግር እየተፈጠረባቸው መኾኑንም ገልጸዋል። አርሶ አደሮች የሚፈልጉት እና የሚቀርበው ሰፊ ልዩነት እንዳለውም ተናግረዋል። ለአርሶ አደሮች በጊዜው እና በበቂ መጠን ማቅረብም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለበጋ መስኖ ልማት ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ ማቅረብ እንደሚገባም ተናግረዋል። የሰላም ሁኔታው የግብዓት አቅርቦትን በተሳካ ሁኔታ ለማዳረስ አስቸጋሪ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል። በተለይም ሩቀት ባለባቸው ወረዳዎች ላይ ግብዓት ለማቅረብ አስቸጋሪ ይኾናል ነው ያሉት።
የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ማዳበሪያን በመጋዘን ውስጥ ማስቀመጥ ለዘረፋ ሊያጋልጠው እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል። የቀበሌ ባለሙያዎች ወደ ሥራ አለመግባታቸውንም ተናግረዋል። ግብርናውን ስኬታማ ለማድረግ ለጸጥታ ሁኔታው ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባም አመላክተዋል። ከአርሶ አደሮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት መፍጠር እና ጥልቅ ውይይት ማድረግ ችግሩን እንደሚያቀለውም ተናግረዋል። አርሶ አደሮች የግብዓት አቅርቦትን እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።
ፍትሐዊ የኾነ የግብዓት አቅርቦት ሊኖር እንደሚገባም አመላክተዋል። አንዳንድ አካባቢዎች የአቅርቦት ምደባ እንደሌላቸውም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!