
አዲስ አበባ: ኅዳር 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቻይና ኩባንያዎች በአፍሪካ ከሚገነቧቸው 1 ሺህ መንደሮች አንዱ የኾነው የኢትዮጵያ መንደሮች ግንባታ ይፋ ሆኗል።
በ51 የአፍሪካ ሀገራት የሚተገበረው 1 ሺህ መንደሮች ግንባታ ባለፈው የዋን ቤልት ሮድ ጉባዔ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዥ ጂምፒንግ ያስተዋወቁት የማኅበራዊ ኀላፊነት ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። በኢትዮጵያ 400 የቻይና ኩባንያዎች የሚገኙ ሲኾን 4 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት እያንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ተገልጿል። ይህ ፕሮጀክትም እነዚህ ካምፓኒዎች የማኀበራዊ ኀላፊነታቸውን የሚወጡበት ነው።
የሠራተኛ እና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ባደረጉት ንግግር ቻይና እና ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ግንኙነት አላቸው ብለዋል። ግንኙነታቸው በማኀበራዊ፣ በምጣኔ ሃብታዊ እና ንግድ ላይ ትስስር አለው ነው ያሉት። ይህ ትስስር አድጎ የቻይና ካምፓኒዎች ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን መወጣት በሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።
ይህ ፕሮጀክት ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቻይና በነበራቸው ቆይታ ግንኙነቱን ለማሳደግ ከቻይና ፕሬዚዳንት ጋር የተስማሙበት አካል ስለመኾኑም ተነግሯል።
በአፍሪካ የቻይና ካምፓኒዎች ጥምረት የማኀበራዊ ኀላፊነት ሊቀመንበር ተወካይ ጂያኦ ቻንሒ እንዳሉት ይኽ ፕሮጀክት ይፋ የኾነው በ3ተኛው የአፍሪካ ቻይና ሮድ ኤንደ ቤልት ጉባዔ ላይ ነው። በፎረሙ ፕሬዚዳንት ዥ ጂምፒንግ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግንኙነታችን ወደ ተጨማሪ አድገት አንዲያመራ መስማማታቸው ይታወሳል።
ይኽ ግንኙነትም ወደ ተቋማዊ እና ጥልቅ ግንኙነት አድጓል። ዛሬ ይፋ የኾነው የኢትዮጵያ መንደሮች ግንባታ ፕሮጀክትም የግንኙነቶቹ የእድገት ማሳያ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የሥራ እድልን በመፍጠር ማኅበራዊ ኀላፊነትን በመወጣት እና በቀጣይ ትውልድ ተስፋ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ሲሉም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱን ስንተገብር ከሴቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመተባበር ይኾናልም ብለዋል።
እኒህ የመኖሪያ መንደሮች ሲገነቡ ሁሉንም ዓይነት ዘመናዊ እና ለኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ባካተተ መልኩ አንደሚገነባም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አንዷለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!