“በከተሞች የሚኖር ሰላም ለሃገሪቱ ጥቅል እድገት የሚኖረዉ ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)

40

ደብረ ብርሃን፡ ኅዳር 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በየትኛውም ዓለም የእድገት እና ስልጣኔ መነሻ ኾነዉ የእድገት አቀጣጣይ ሚናቸዉን የሚወጡት ከተሞች ናቸዉ፡፡

በከተሞች የሚኖር ሰላም የትኛውንም ክፍል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንካቱ አይቀርም፡፡ ከከተሞች ውጭ ባለው ክፍል ላይ የተሻሻሉ ቴክኖሎጅዎችን ለማዳረስ፣ መሠረተ ልማት ለመዘርጋት፣ በአርሶ አደሩ ቀዬ ምርትን ለመጨመር እና ሌሎችን ተግባራትን ለማከናወን የከተሞች ሰላም መኾን እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ(ዶ.ር) በከተሞች ሰላማዊነት እና ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ከተሞች የእድገት የስበት ማዕከል በመኾናቸዉ በተለያዩ ከተሞች ያለው የሰላም ሁኔታ ለሃገሪቱ ጥቅል እድገት የሚኖረው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ብለዋል።

ሰላም በየትኛውም አካባቢ ያስፈልገናል ያሉት ዶክተር አሕመዲን ለዚህ ደግሞ የባለቤትነቱን ኀላፊነት ሁላችንም ልንወስደው የሚገባ ተግባር ስለመኾኑ አንስተዋል፡፡

ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ ከተሞች የግብይት ማዕከል ኾነው የሚያገለግሉ ከፍተኛ ግብር የሚሰበሰብባቸው ናቸው። ዶክተር አሕመዲን ለሥርዓተ መንግሥት መጽናት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው ነው ያሉት፡፡

ይህንን በውል በመረዳትም በከተሞችም ይኹን በሌሎች አካባቢዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሰላማዊ ሂደትን ሊከተሉ ይገባል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ችግር ከተሞች የተለመደ የልማት ተግባራቸውን ለማከናወን እንከን ገጥሟቸዋል ያሉት ዶክተር አሕመዲን ለዚህ ማሳያ የሚኾነውም ከከተሞች የሚሰበሰበው ግብር አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መኾኑን አንስተዋል፡፡

በከተሞች የሚሠሩ የትኛዉም ዓይነት የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ምንጫቸው ከከተሞች የሚሰበሰብ ግብር በመሆኑ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ እንዲከፍሉም አሳስበዋል፡፡

እስካሁን በነበረው የሰላም መደፍረስ ችግር ምክንያት እንከን የገጠማቸውን ከተሞች በፍጥነት ወደ ሥራ ማስገባት ይገባል ተብሏል። የተለመደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እና ነዋሪዎቻቸው የሚፈልጓቸውን የልማት አውታሮች ለመገንባት በእቅድ ላይ የተመሠረተ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑም ዶክተር አህመዲን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተገዛውን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶአደሮች ለማድረስ ሁሉም ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ
Next articleበብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በቻይና የዱጂያንግያን የመስኖ ፕሮጀክትን ጎበኘ።