“የተገዛውን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶአደሮች ለማድረስ ሁሉም ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

59

ባሕር ዳር: ኅዳር 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን በተመለከተ በየደረጃው ከሚገኙ መሪዎች ጋር እተወያየ ነው። ውይይቱ በአፈር ማደበሪያ አቅርቦት የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ በወቅቱ ማቅረብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ነው። በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳሕሉን (ዶ.ር) ጨምሮ የቢሮው እና የዞን የግብርና የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን እና ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ማብራሪያ የሰጡት የቢሮው የግብርና ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ ባለፈው ዓመት የነበረውን ችግር ለመፍታት የአፈር ማዳበሪያ ግዢ አስቀድሞ መፈጸሙን አመላክተዋል። የተገዛውን የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብና ለማሰራጨት ችግር እየገጠመ መኾኑንም ተናግረዋል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ደግሞ ለስርጭቱ መሰናክል ኾኗል ነው የተባለው።

የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም የተናገሩት ዳይሬክተሯ አቅርቦቱ በሚፈለገው ልክ አለመኾኑንም አንስተዋል። በዚህ ዓመት ለአማራ ክልል የተገዛውን 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ተደራሽ ማድረግ ይገባናልም ብለዋል።

በ2015/16 የምርት ዘመን ከገጠመው ችግር ትምህርት በመውሰድ በ2016/17 የምርት ዘመን ችግር እንዳይኖር መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

ጥንካሬዎችን በማጉላት፣ ጉድለቶችም በማረም የግብዓት አቅርቦት ላይ በትኩረት መሥራት ይገባልም ብለዋል።

ለ2016/17 የምርት ዘመን ከባለፈው ዓመት ከፍተኛ ጭማሪ ያለው የአፈር ማዳበሪያ ግዢ መፈጸሙን ገልፀዋል። የአፈር ማደበሪያ በወቅቱ እንዲደርስ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።

ሕገ ወጥ የግብዓት ዝውውርን ከወትሮው በተለየ በትኩረት መከታተል እና መግራት ይገባልም ብለዋል። የግብዓት አቅርቦት እና ሥርጭት ውጤታማ እንዲኾን በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች እና ባለሙያዎች ኀላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቻይና ብሔራዊ ኮንግረስ ምክትል ሊቀ መንበር ሎሳንግ ጂያልትሰን አዲስ አበባ ገቡ።
Next article“በከተሞች የሚኖር ሰላም ለሃገሪቱ ጥቅል እድገት የሚኖረዉ ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)