“የጋራ ብሔራዊ ትርክት መገንባት ተገቢ ነው” አደም ፋራህ

418

ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለዘመናት ከውጪ እና ከውስጥ በሚነሳ ጠላት እረፍት አልባ ኾና ዘመናትን ያስቆጠረችው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ጸንታ የመዝለቋ ምስጢር ከራሳቸው በላይ ሀገራቸውን፤ ከጥቅማቸው በላይ ወገኖቻቸውን የሚስቀድሙ ልጆች ባለቤት መኾኗ ነው፡፡ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ዘመናትን አልፋ አሁን ላይ ስትደርስ እልፍ ሕይዎት ተገብሮ እና መራር መሥዋዕትነት ተከፍሎ ነው፡፡

ፈተናዎቿን በጽናት እና መሰናክሎቿን በስልት ያለፈችው የትናንቷ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በዚህ ትውልድ ዘመን አትፈርስም ሲባልም የአባቶቹን ተጋድሎ የወረሰ ትውልድ ባለቤት ስለኾነች ነው፡፡ ሀገርን ከነድንበር፤ ታሪክን ከነክብር ለማስቀጠል ግን ውስጣዊ አንድነትን እና የጋራ ሀገራዊ እሴትን ማስቀጠል ይጠይቃል፡፡

በዘመነ ቅኝ ግዛት ምሥራቅ አፍሪካውያኑ የጦር ምትሃተኞቹ ኢትዮጵያውያን ነጻነታቸውን በክንዳቸው ቢያስከብሩም ቅኝ ገዥዎቹ ምዕራባዊያን ወራሪዎች በአካባቢው ዘርተውት ያለፉት አሚካላ አሁንም ድረስ ዋጋ እያስከፈለ ዘልቋል፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአንድ ከቆሙ ለዓላማቸው መሳካት እንቅፋት እንደኾኑ ማየታቸው በብሔር እና በዘር፤ በሃይማኖት እና በማንነት መነጣጠል ነገ ለሚያልሟት ደካማ ኢትዮጵያ ፍቱን መድኃኒት ነው ብለው አሰቡት፡፡

ምዕራባዊያኑ ቅኝ ገዥዎች በዚያን ዘመን የዘሩት የሃሳብ እንክርዳድ አሁንም ድረስ ከገብሱ መካከል በቅሎ አረሙ ከምድረ ኢትዮጵያ መነቀል አልቻለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየጎላ የመጣው የዜጎች መፈናቀል፣ ግድያ እና ማሳደድ አንድ ከሚያደርጉ እና ከሚያስተሳስሩ የጋራ ታሪኮች ይልቅ በልዩነት ላይ የተመሰረቱ የተናጠል ትርክቶች እየገዘፉ መምጣታቸው ነው፡፡

ቀደምት ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንዳቸው ለዘመናት የሀገራቸውን ክብር እና ሉዓላዊነት አጽንተው ቆይተዋል ያሉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የጽሕፈት ቤት ኅላፊ አደም ፋራህ በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን የሀገርን እና የሕዝብን ጥቅም የሚያስከብር ሥልጡን ፖለቲካ መገንባት አልቻልንም ነበር ብለዋል፡፡ ለሁሉም የምትመችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት እና የሕዝብን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከር “የጋራ ብሔራዊ ትርክት መገንባት ተገቢ ነው” ብለዋል፡፡

ፓርቲያቸው በቀጣይ ጊዜያት ገዥ እና ታላላቅ ትርክቶችን የመገንባት አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደኾነ ያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ብሔራዊ ትርክቶች በጋራ ጥቅም፣ ታሪክ እና በመጻዒዋ ኢትዮጵያ ፍላጎት ላይ የሚመሠረት በመኾኑ ለትውልድ ምንዳ ይኾናል ብለዋል፡፡ በየአካባቢው ጎልተው የሚሰሙ ነጠላ ትርክቶች ከሰፈር የመውጣት አቅም የላቸውም፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ታላቅ ሀገር ለመገንባት ያለንን ራዕይ ስለሚያሰናክሉ ነጠላ ትርክቶችን መሻገር እና የትውልድን እዳ ማቃለል ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡

የታላቅ እና ገዥ ትርክት ትግበራው መርህ ከፓርቲው አባላት መጀመር ይኖርበታል ያሉት አቶ አደም ፋራህ የጋራ የኾነ፣ የሚያስተሳስር እና ነገን የሚገነባ ገዥ ትርክት ለመገንባት የፓርቲው አመራሮች እና አባላት ግንባር ቀደም ሊኾኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡ በልጆቻችን ላይ እንዲንጸባረቅ የምንፈልገው ግብረ ገብነት ከሁሉም ቀድሞ በፓርቲው አባላት እና መሪዎች ዘንድ ሊገለጥ ይገባል፤ ለዚህም በትጋት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት አለመዳበሩ፣ የፍጹማዊ አንድነት እና ልዩነት ትርክት መስፋፋቱ እና ኋላቀር የፖለቲካ አካሄድ መኖሩ የጋራ ትርክት የመገንባት ሂደትን ይፈትነዋል ብለዋል፡፡ የፓርቲው አመራር እና አባላትም ለፈተናዎች ሳይበገሩ የሚፈለገውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ጠንካራ ትግል ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡

ብልጽግና ላስቀመጣቸው ሀገራዊ ራዕይ መሳካት ሁሉም የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች የዓላማ ጽናት፣ የአመለካካት እና የተግባር አንድነት በመያዝ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ በሂደቱም ከስህተቱ የማይማር፣ የጋራ እሴቶችን እና የፓርቲውን መርሕን የማያከብር አመራርም ኾነ አባል ተገቢውን ማጥራት በማድረግ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡ የማጥራት ሥራው ጊዜ ወሳጅ መኾኑን መረዳት ተገቢ እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ444 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የትምህርት ግብዓቶችን ለትምህርት ቤቶች ለማሰራጨት እየሠራ መኾኑን ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
Next articleዋልያዎቹ ዛሬ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሴራሊዮን ጋር ይጫዎታሉ።