
ከ444 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የትምህርት ግብዓቶችን ለትምህርት ቤቶች ለማሰራጨት እየሠራ መኾኑን ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
ባሕር ዳር: ሕዳር 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በኮበል ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር እየተሠሩ የሚገኙ የትምህርት ግብዓቶችን ተመልክተዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ከሚሠራቸው ሥራዎች የትምህርት ግብዓት ማሟላት አንዱ ነው። ቢሮው ባለፉት ዓመታት በረጅ ድርጅቶች እና በክልሉ መንግሥት የተለያዩ የትምህርት ግብዓቶችን እያቀረበ እንደሚገኝ ዶክተር ሙሉነሽ ገልጸዋል። አሁን ላይም ከ444 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ከ46 ሺህ በላይ የተማሪዎች መቀመጫ፣ ጥቁር ሰሌዳ፣ የመምህራን መቀመጫ ወንበር እና ጠረጴዛ ለኮበል ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር ውል ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል።
ቢሮው ከዚህ በፊትም ትምህርት ቤቶች ያሉባቸውን ችግሮች መሠረት በማድረግ ግብዓት ሲያቀርብ መቆየቱን ገልጸዋል። ለትምህርት ቤቶች የሚደረገው የግብዓት ማሟላት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። ቢሮው ረጅ ድርጅቶችን በማሳተፍ ጭምር 100 ሚሊዮን የሚያወጣ ደብተር ጨረታ መውጣቱን ገልጸዋል።
ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የትምህርት ቁሳቁስም ረጅ ድርጅቶ ለቢሮው ማስረከባቸውን ተናግረዋል። የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ጉዳይ አለመኾኑን ያነሱት ቢሮ ኀላፊዋ ረጅ ድርጅቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኮበል ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ መላክ ዓለሙ እንዳሉት አሁን ላይ ከትምህርት ቢሮ ውል በመውሰድ 44 ሺህ 600 የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር፣ 1 ሺህ ጥቁር ሰሌዳ፣ 1 ሺህ የመምህራን ወንበር እና የመምህራን ጠረጴዛ በ90 ቀናት ለማድረስ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ማኅበሩ ሥራ በጀመረ በ28 ቀናት ውስጥ ከአጠቃላይ ሥራው 36 በመቶ ማከናወኑን አንስተዋል። በተቀመጠለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ከነበረው የሰው ኀይል በተጨማሪ ለ100 ተጨማሪ የሰው ኀይል በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል። ማኅበሩ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ20 ሺህ በላይ ጥቁር ሰሌዳ፣ የተማሪ መቀመጫ፣ የመምህራን ወንበርና ጠረጴዛ የመሳሰሉ የትምህርት ቁሳቁስን ሠርቶ ማስረከቡን ገልጸዋል። ማኅበሩም ከዚህ በፊት ከ750 ሺህ በላይ ብር የሚያወጡ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል። ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!