
ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች በክልሉ ወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ ዙሪያ ተወያይተዋል።
ውይይቱ የአማራ ክልል ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ እና ችግሮችን በመነጋገር ለመፍታት የሚያስችል ነው ተብሏል። በውይይቱ የከተማው ነዋሪዎች እና በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች እየተሳተፉ ነው።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አስተያየት ሰጭዎች መንግሥት ሰላማቸውን እንዲያስጠብቅላቸው ጠይቀዋል። በየጊዜው በሚደረግ ውይይት ችግሮች ሊፈቱ ስለሚችሉ ተቀራርቦ መነጋገር ተገቢ ነው ብለዋል።
ሰላም ሊመጣ የሚችለው በጋራ በመወያየት እና በመመካከር ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በየጊዜው ውይይት ማድረግ ብቻ ሳይኾን ለውይይቱ መፍትሔ ይዞ መቅረብ ይገባልም ነው የተባለው።
አስተያየት ሰጪዎቹ በአማራ ክልል በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች መድረሳቸውን ገልጸዋል።
የነበሩ የተሳሳቱ አመለካከቶች፣ አሠራሮች፣ አገልግሎት አሠጣጦች ሊሻሻሉ ይገባል። ሕዝቡም መፍትሔ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል። ጦርነት አስፋላጊ አይደለም የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ “ከመለያየት ወጥተን አንድነትን፤ ከመገዳደል ወጥተን መረዳዳትን ልናሳድግ ይገባል” ነው ያሉት።
በክልሉ የተከሰተው የኑሮ ውድነት መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል።
ሰላም ባለመኖሩ የኑሮ ውድነት ተባብሶ በልተን ለማደር ተቸግረናል፤ ችግር ላይ ነው ያለነው፤ መንግሥት ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን እና ደላላውን ሊቆጣጠር ይገባልም ብለዋል።
ውይይቱን የመሩት በቢሮ ኀላፊ ደረጃ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አማካሪ ግዛት አብዬ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት በተለያዩ ቦታዎች ውይይት እያደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።
የክልሉ አጠቃላይ ችግሮች የሚፈቱበትን ምቹ ሁኔታ መንግሥት እያመቻቸ መኾኑንም አቶ ግዛት ተናግረዋል።
በክልሉ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ አቅሞች በክልሉ ሕዝብ እጅ እንዳለ ገልጸዋል።
በክልሉ የተከሰተው ችግር በማኅበራዊ፣ በምጣኔ ሃብታዊ እና በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ችግር መፍጠሩን ጠቅሰው ይህን የጸጥታ ችግር ሕዝቡ ለሰላም ዘብ በመቆም ሊከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተፈጠረው አለመረጋጋት የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች እንዲቋረጡ መደረጉንም ጠቁመዋል።
ሕዝቡ በብልሹ አሠራር የተተበተቡ አካላትን ከመንግሥት ጎን በመቆም መታገል እንዳለበትም አሳስበዋል።
“የሰላሙ ባለቤት ሕዝብ ነው” ያሉት አቶ ግዛት ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ነጻነቱን ሊያስከብር ይገባልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:-ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!