
ባሕር ዳር: ኀዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ቀበሌዎች የሕዝብ ውይይት ተደርጓል። የውይይቱ ዓላማ ያጋጠመውን የሰላም ችግር በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ለመፍታት መኾኑን የውይይቱ አስተባባሪዎች ገልጸዋል።
በውይይቶቹ ለሰላም እጦቱ የሕዝቡ የቆዩ ጥያቄዎች አለመመለስ እና ወቅታዊ ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘታቸው መኾኑ ተነስቷል። የመፍትሄ ሃሳብም ተመላክቷል።
የቀበሌ 08 ነዋሪ አቶ ጥላሁን አደላ አሁን ያለው ችግር አለመመካከርና አንድነት የማጣት መኾኑን ገልጸዋል። ”ሕዝብን በአንድነት ሊመራን እና ሊያግባባ የሚችል መሪ ያስፈልጋል” ብለዋል። የሰላም እጦቱ መፍትሄ መመካከርና መግባባት መኾኑን ጠቁመዋል።
”ለዚህ ችግር ያበቃን ሲንከባለል የቆየ ችግርና ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱ ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ለምለም አማረ ናቸው። የኑሮ ውድነት እና የመኖሪያ ቤት ችግር ተጠቃሽ መኾናቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ለምለም ኅብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች አወያይቶ ምላሽ አለመሰጠቱ ችግሩን እንዳከፋውም አክለዋል። ”ሁሉቱም ወንድሞቻችን ናቸው፤ መፍትሄውም ሁለቱንም አካላት አቅርቦ ማወያየት ነው” ሲሉም መፍትሄ ያሉትን አመላክተዋል።
የግሽ አባይ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገበያው መኳንንት በሁሉም ቀጠናዎች ከሕዝብ ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ ያነሳቸውን ሃሳቦች ሰምተናል፤ በኛ አቅም የሚፈቱትን እንፈታለን፤ ከኛ ሥልጣን በላይ ያሉትን ጥያቄዎችም ለሚመለከተው የበላይ አካል እናቀርባለን ብለዋል።
ሕዝቡ ከጸጥታ ኀይሎች ጋር ተባብሮ የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ዝግጁ መኾኑን አስተያየት ሰጪዎች የገለጹ ሲኾን ለዚሁ ዓላማም አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!