
ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም የፕሪቶሪያ ስምምነት፣ የዲፕሎማሲ እና የወደብ ጉዳይ ትኩረት ያደረጉባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
የፕሪቶሪያ ስምምነት ለእናቶች እፎይታ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡ ተጨማሪ ሰዎች እንዳይሞቱ አድርጓል፤ በገባነው ቃል መሠረት አገልግሎት እንዲጀመር አድርገናል፤ የክልሉ መንግሥት ተቋቁሟል፡፡ በርካታ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገን ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በውይይት እንደሚፈቱ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡
ዲፕሎማሲ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ከሌሎች ጋር በሚኖር ትብብር እና ስምምነት የሚፈጸም መኾኑን አንስተዋል፡፡ ብሔራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነት፣ መልካዓ ምድራዊ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዉ ትሩፋቶች እና ጎረቤቶችን ያቀፈ ፖሊሲ እንከተላለን ነው ያሉት፡፡
ብሪክስ ውስጥ ስንገባ ሌሎችን ለመጉዳት እና ሌሎችን ለመጥቀም አይደለምም ብለዋል፡፡ ብሪክስ የገባነው ሌላውን ጠልተን እና ሌላውን ተቃውመን አይደለም ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ከሩቁም ከቅርቡም፣ ከምሥራቁም ከምዕራቡም ተስማምታና ተጋግዛ ማደግን የምታስቀድም ሀገር መኾኗንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሌሎችን ለመጉዳት እንደማታስብም ገልጸዋል፡፡ ወደብን በሚመለከት ብዙ አይነት ንግግሮች፣ ትንበያዎች፣ ሤራዎች እና ትንተናዎች መኖራቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም እንዲገነዘብ የምንፈልገው የእኛን ፍላጎትና ችግር ነው ብለዋል፡፡ ከዛሬ ሰላሳ ዓመታት ገደማ ኢትዮጵያ የሁለት ወደብ ባለቤቶች እንደነበረችም አንስተዋል፡፡ ሁለት ወደብ በነበራት ጊዜ የሕዝብ ቁጥሯ እና እድገቷ አሁን ላይ እንዳለው እንዳልነበር ነው የተናገሩት፡፡
በጊዜ ሂደት ሁለት ወደብ የነበራት ሀገር በንግድ ወደብ ዝቅ ማለቷን እና ከኤርትራ ጋር በነበረው ግጭት ደግሞ የጅቡቲ ወደብ ብቻ ቀርቷት እንደቆዬ ነው የገለጹት፡፡ ጅቡቲ ወደብ እንድንጠቀም በማድረጓ ዕውቅና እንሰጣለን ነው ያሉት፡፡
በቀጣናው ባለው ፖለቲካ ምክንያት የእኛ ስጋት በጅቡቲ ወደብ ላይ ችግር ቢፈጠር እኛ ምን እንኾናለን የሚል ነው። የጅቡቲ ወደብ ቢያቆም የኢትዮጵያን ሕዝብ ምን እናደርገዋለን የሚል ነውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወደብ ጉዳይን በተመለከተ ከፓርላማ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ።
ቀይ ባሕር አያስፈልገንም የሚል ኃይል የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛ ስንፈልገው ለምን ነውር ኾነ? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ቀይ ባሕር ብቸኛ መተንፈሻችን ነውም ብለዋል፡፡ ቀደም ብሎም የባሕር ኃይል ስንገነባ ዋና አጀንዳችን የባሕር ኃይል እንፈልጋለን ማለታችን ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡
በወደብ ጥያቄው የኤርትራን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ነው የሚሉ አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስሩ ሕዳሴን ስንገነባ የሱዳንን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ነው ወይ ? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሕዳሴን የገነባነው ኃይል ለማመንጨት እና ውኃውን ለክተን ለመላክ ነው፣ ወንድሞቻችን እንዲጎዱ አንፈልግም፤ ቀይ ባሕርም እንዲሁ ነው ብለዋል፡፡
የማንንም ሉዓላዊነት የመንካትም ኾነ ማንንም የመውረር ፍላጎት የለንም በቢዝነስ ሕግ ግን የማያወላዳ ምርጫ እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡ በዚህ ከእኛ በላይ መጨነቅ ያለባቸው ወንድሞቻችን ናቸውም ብለዋል፡፡ አጀንዳውን በስክነት ማየት እና መነጋገር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ እንነጋገር ችግራችንን ተረዱን እንጂ ወደ ግጭት እንግባ አላልንም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሕግ እና ሰላም ውጭ ያልተገባትን ጥያቄ ጠይቃ ከኾነ እንተዋለን ነው ያሉት፡፡ በውይይት ካልተፈታ ምን ሊያጋጥም እንደሚችል መገመት ይቻላል፤ ወደ የትኛውም ሀገር ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለንም። የማንንም ሉዓላዊነት አንነካም፤ እያልን ያለነው ያለንን እናጋራ እናንተም አጋሩን ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን የኾነ ኃይል ተነስቶ ጥቃት ያደርስባታል የሚል ስጋት የለንም፤ ኢትዮጵያን የመታደግ ከበቂ በላይ አቅም አለን ብለዋል በማብራሪያቸው፡፡
የወደብ ጉዳይ አዲስ አጀንዳ አለመኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የወደብ ጉዳይ ነገን ታሳቢ ያደረገና የልጆቻችን እጣ ፈንታ ግምት ውስጥ ያስገባ ነውም ብለዋል፡፡ ችግሩ ከመምጣቱ በፊት መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የዓለም መንግሥታትም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳይጎዳ ማገዝ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ያልተገባንን ጠይቀን ከኾነም አስተካክሉ ይበሉን ብለዋል፡፡
የምንወርረውም ኾነ የምንወጋው ሀገር የለም፣ በጥያቄው ግን አናፍርም፣ ምክንያቱም የልጆቻችን ሕይወት መታደግ አለብን ነው ያሉት፡፡ ጥያቄውን እንደ ወንጀል ማሰብ ተገቢ አለመኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!