
ባሕር ዳር: ሕዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ከምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ፣ ከኑሮ ውድነት እና ከዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ አሉ ባሏቸው ችግሮች ዙሪያ ያነሷቸውን ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት እንደየትኛውም ዓለም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት ተከስቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሮና፣ ግጭት እና የዓለም ንግድ ሚዛን መዛባት ለችግሩ መባባስ ምክንያት ኾኗል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ኾኖ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ጥቅል ሀገራዊ ገቢዋ በእጥፍ አድጓል ነው ያሉት፡፡ ይኽም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተስተዋለ እድገት እንደኾነ ጠቅሰው የተከተልነው “ከግሬይ ወደ ግሪን ኢኮኖሚ ሽግግር” የተስተካከለ ምጣኔ ሃብታዊ መስመር ነበር ብለዋል፡፡
ወደ መንበረ መንግሥትነት ስንመጣ የኢትዮጵያ ጥቅል ሀገራዊ እድገት 84 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁናዊ የሀገሪቷ ጥቅል እድገት 164 ቢሊዮን ደርሷል ነው ያሉት፡፡ ጥቅል ሀገራዊ እድገቱን በሚመለከት መንግሥት ብቻ ሳይኾን የውጭ ተቋማት እና ድርጅቶችም ያረጋገጡት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ፈጣን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል ግንባር ቀደም ኾናለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምሳሌ ያክል ከአምስት ዓመት በፊት 882 ዶላር የነበረው የግለሰቦች ነፍስ ወከፍ ገቢ አሁን ላይ 1 ሺህ 549 ዶላር ደርሷል ብለዋል፡፡ ሌሎች ምጣኔ ሃብታዊ ለውጦችም የሚያመላክቱት ፈጣን እድገት እያስመዘገበች መኾኑን ነው ብለዋል፡፡
ምጣኔ ሃብታዊ እድገቱ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያ ችግር ፈትቷል ማለት ሳይኾን ለማደግ ተስፋ ያላት እና በቀላሉ መለወጥ የምትችል ሀገር ለመገንባት መሠረት እያስቀመጥን መኾኑን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ልጆቻችን ያስቀመጥንላቸውን መሠረት አድርገው የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ይገነባሉ ነው ያሉት፡፡ የነበርንበት ጥልቅ ድህነት አሁን እሱን ማድረግ የምንችልበት አቅም እንድንፈጥር የሚያስችል አልኾነም ብለዋል፡፡
ያለፈው ዓመት የግብርና እድገት 6 ነጥብ 3 በመቶ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄ እድገት እንዲመዘገብ መንግሥት በርካታ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ አድርጓል ብለዋል፡፡ በተለይም የሰብል ምርት 7 ነጥብ 1 በመቶ አድጓል ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት 20 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ 600 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ብለዋል። በተያዘው የምርት ዘመንም ከ22 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ ከ800 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል፡፡
የክረምት ሥራዎቻችን እቅዶቻችንን እንደምናሳካ አመላካች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበጋ የግብርና ሥራዎች “ከሦስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የበጋ ስንዴ ለማምረት ይታረሳል” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን