
ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ተጨማሪ ማብራሪያዎችን እየሰጡ ነው።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ በጥቅሉ 6 ነጥብ 9 በመቶ እድገት መመዝገቡን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ከ12 በመቶ በላይ ከፍተኛ እድገት ተመዝግቧል ብለዋል። በግንባታ ዘርፉ 7 ነጥብ 1፣ በምርት ዘርፉ ደግሞ ከ7 በመቶ በላይ እድገት ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በተለይም የምርት ዘርፉ “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚለው እንቅስቃሴ 47 በመቶ የነበረው የፋብሪካዎች ድምር የማምረት አቅም ወደ 55 በመቶ አድጓል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳ እና በኬሚካል ምርት ዘርፎችም እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ደካማ የማምረት አቅም ያላቸውን ፋብሪካዎች በመደገፍ እና ጠንካራዎችንም ካላቸው አቅም በላይ እንዲያመርቱ በማጠናከር አሁን ባሉት ፋብሪካዎች ብቻ ለሀገር የሚበቃ ምርት ለማምረት እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጠቁመዋል።
የውጭ ምንዛሬ አቅምን የሚያግዙ ተኪ ምርቶችን በትኩረት ለማምረት ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል። በዚህም የድንጋይ ከሰል እና የቢራ ገብስን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል ብለዋል። የሚመረቱ የሀገር ውስጥ ፍጆታ ምርቶች ከነበሩበት 30 በመቶ ወደ 38 በመቶ ማድረስ መቻሉንም አስረድተዋል።
የአገልግሎት ዘርፉም እድገት ማስመዝገቡን በምክር ቤቱ አንስተዋል። በተለይም የመጓጓዣ እና የኮምዩኒኬሽን ዘርፉ ሰፋ ያለ እድገት የተመዘገበበት ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም የእድገቱ ዋነኛ አመላካቾች እንደኾኑም ተነስቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆቴል ቱሪዝሙ መነቃቃት እና መሻሻል ታይቶበታል ብለዋል። የበለጠ ተግቶ እና በታማኝነት በመሥራት ከዚህ በላይ እድገት ማስመዝገብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!