“የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር እዳ እየቀነሰ 14 ነጥብ 8 በመቶ ደርሷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

34

ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ እዳዋን ለመቀነስ እየሠራች መኾኗን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት እዳን ለመቀነስ ሰፋፊ ሥራዎች መሠራታቸውን አስታውቀዋል፡፡ መንግሥታቸው ጥቅል እዳ መረከቡን ተናግረዋል፡፡ በዓለም መንግሥታት እየዞርን እዳችሁን አሸጋግሩልን የምንለው እኛ የተበደርነው እዳ አይደለም፣ የቀደመው መንግሥት ምን ላይ እንዳዋለው የማናወቅውን የገንዘብ እዳ እንደ ፖለቲካ እዳ መክፈል ስላለብን ነው የምደራደረው ብለዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠራው ሰፊ ሥራ የሀገር ውስጡን ጨምሮ የኢትዮጵያ አጠቃላይ እዳ 31 በመቶ ገደማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ሀገር እዳችን እየቀነሰ 14 ነጥብ 8 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት፡፡ በተሠሩት ሥራዎች እዳ መቀነሱን እና በሚቀጥሉት ዓመታትም እዳን ለመቀነስ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳለባት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውጭ ምንዛሬ የሚገኝ ገቢን ለማሳደግ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ በውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ገቢ መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡ ካለው አቅምና ፍላጎት አንጻር የተገኘው ውጤት በቂ አለመኾኑም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በኑሮ ውድነት ዜጎች እየተቸገሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ያልታዬ የዋጋ ግሽበት በዓለም አቀፍ ደረጃ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ የመጣው ዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ገቢ አለመጣጣም ለዜጎች ፈተና መኾኑን ነው ያነሱት፡፡

የእዳ ክፍያ መጨመርም የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እንዳደረገው ነው የተናገሩት፡፡ የኮሮና ቫይረስ እና ሌሎች ችግሮች እንደ ሀገር ጫና መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 3 ነጥብ 9 በመቶ የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ500 ሺህ በላይ ለኾኑ ወጣቶች በሩብ ዓመቱ የሥራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል። 100 ሺህ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ የውጪ ሀገር የሥራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ልጆቻችን በሕይወት ፈተና ከሚወድቁ በአንድ ዘመን ፈተና ቢወድቁ ይሻላል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“47 በመቶ የነበረው የፋብሪካዎች ድምር የማምረት አቅም ወደ 55 በመቶ አድጓል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)