
ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካተኮሩባቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው የትምህርት ሥርዓቱ ጉዳይ ነው፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ዘርፈ ብዙ ስብራት እንደላበትም ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት የትምህርት ጥራቱ መውደቅ ኢትዮጵያን እየጎዳት መኾኑን ስናነሳ ቆይተናል ነው ያሉት፡፡
በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የደረሰውን ስብራት ለመጠገን ሥርዓተ ትምህርት መቀየር፣ የመምህራንን አቅም መገንባት፣ የትምህርት አሥተዳደር ሥርዓት መቀየር፣ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የፈተና ሥርዓቱን ማሻሻል፣ የተማሪዎች ምገባ መጀመር እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ማስፋቱን ቀንሰው ጥራቱን እናስፋፋ በሚል ሥንሠራ ቆይተናል ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በርካታ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ማስፋፋታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ትምህርትን ለማሻሻል መሠረቱን ማሳመር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በፈተና ሥርዓቱ ላይ የአፈታተን ሥርዓቱ በመቀየሩ ምክንያት ውጤት ዝቅ ማለቱንም ተናግረዋል፡፡ የውጤቱ ዝቅተኛ መኾንም የሚጠበቅ እንደነበር ነው የገለጹት፡፡
ውጤቱ በአንድ ጊዜ እንደሚፈለገው እንደማይኾንም ተናግረዋል፡፡
የተማሪዎች ውጤት ቤተሰብን እንዳሳዘነም ገልጸዋል፡፡ “ልጆቻችን በሕይወት ፈተና ከሚወድቁ በአንድ ዘመን ፈተና ቢወድቁ ይሻላልም” ብለዋል፡፡ የአንድ ዘመን ፈተና ማስተማሪያ እና መወንጨፊያ ሊኾን እንደሚችል በማንሳት፡፡
ብዙዎቹ ተማሪዎች ጥቂት ቢሠራባቸው ሀገር መለወጥ ይችላሉም ብለዋል፡፡ አሁን ላይ በፈተና አላለፉም ማለት ወድቀው ቀሩ ማለት አለመኾኑንምም ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ተማሪዎችን የሚጠቅም፣ ሀገርን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
አሁን ባለው ኹኔታ ከቀጠልን የኢትዮጵያ የትምህርት ስብራት አይጠገንም፤ ቆንጠጥ ብለን ማሻሻል ይጠበቅብናልም ብለዋል፡፡ ለውጡ ፈተና ብቻ ሳይኾን ሁሉንም ያቀፈ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ በጥቁት ጊዜ ለውጥ እንደሚያመጣም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!