
ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ሕብረ ብሔራዊ ሠራዊት መገንባቱን ገልጸዋል፡፡ የተገነባው ሠራዊት በትጥቅ ብቃት ብቻ ሳይኾን ሀገሩን የሚወድ እና በሀገር ፍቅር ጭምር የተገነባ ነውም ብለዋል፡፡
ሠራዊቱ ኢትዮጵያን አስቀድሞ ይሠራል ነው ያሉት፡፡ ሠራዊቱ በሶማሊያ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በሌሎች ክልሎች ኢትዮጵያን እያስቀደመ ሞቷል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን የሚገዳደር ኃይል በተነሳ ቁጥር ኢትዮጵያን እያስቀደመ መሞቱንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ኃይል ከየትም ቢነሳ ኢትዮያዊነትን የሚያስቀድም፣ የማይታገስ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ሠራዊቱ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን ያስቀድማል ነው ያሉት፡፡ በውጭ ኃይሎች አይዟችሁ ባይነት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሁሉን አቅፋ የምትኖር፣ ሁሉ ያላት ሀገር መኾኗን የተናገሩት ዶክትር ዐቢይ በውጭ ኃይሎች የሚደገፉ ኃይሎች ኢትዮጵያን ባልተገባ መንገድ እንድትታይ እያደረጉ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ መንግሥትን በጦርነት መጣል አይቻልም ብለዋል፡፡ ጦርነትን አቁመን እንወያይ፣ እንመካከር፣ ችግሮቻችን በጋራ እንፍታ፣ ጠያቂ ብቻ ሳይኾን መፍትሔ አፋላላጊ እንሁን፤ ይህ ለኢትዮጵያ ያዋጣል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል ሚዲያን በተመለከተ ሀሳብ ሰጥተዋል። ሚዲያ አጥፊም አልሚም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ያለው የሚዲያ ድባብ ገመና አልባ፣ የሚነገርና የማይነገር የማያውቅ፣ የሀገርና የሕዝብ ጥቅም የማያስከበር መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በታሪክ የሚያሳፍር ሥራ ላለመሥራት ሚዲያዎች መጠንቀቅ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሚዲያዎች መኖራቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚዲያዎች ዙሪያ የሚና መደበላለቅ አዝማሚያ መኖሩንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያልተገቡ የሚዲያ ዘመቻዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሚደያዎች ለመደመጥ ውሸት እና ሤራ እንደሚያመርቱም ገልጸዋል፡፡
መንቃት ያለበት ሰሚዉ ነው፤ መደመጥ ያለበትን መለየት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ሚዲያዎች በሕግ አግባብ እንዲገሩ ይደረጋልም ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ በከፍተኛ ትጋት የሚሠሩ ሚዲያዎች ስለመኖራቸውንም አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!