
አዲስ አበባ: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን በማስመልከት የመገናኛ ብዙኃን የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዓላማው ልምድ፣ ተሞክሮ እና መልካም ባሕሎችን በመለዋወጥ ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ነው ብለዋል። ሕዝቦችን ለዘላቂ ሰላም፣ ለልማትና ለኢኮኖሚ እድገት ለማነሳሳትም ያገለግላል ብለዋል።
በዓሉ ባለፉት ዓመታት ሲከበር መቆየቱንም አፈ ጉባዔው አንስተዋል። ሕዝቦች ለረጅም ዘመናት ይዘውት የቆዩትን አብሮነት እንዲያጎለብቱ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን እንዲያጸኑ እና በሕገ መንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲፈጠሩ የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ በእነዚህም ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡
“በዓሉ ለብዝኃነት ዕውቅና ለመስጠት፣ እኩልነትን ለማስተናገድ፣ አንድነትን እና ሰላምን ለማጽናት ያግዛልም” ብለዋል። ኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያን ለመገንባትም ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል አፈ ጉባዔው።
የዘንድሮው በዓል በየደረጃው ሲከበር የሕዝቦች አንድነትና ትስስር እንዲረጋገጥ በማድረግ እንዲሁም የሀገሪቱ ሰላም እና አንድነት ተጠብቆ ከነሙሉ ክብሯ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጠንካራ ሥራ የሚሠራበት እና ትኩረት የሚደረግበት ይኾናልም ነው ያሉት፡፡
አፈ ጉባኤው በዓሉ ሲከበር ሀገራዊ አንድነትን የሚተክል የመገናኛ ብዙኀን አገልግሎት እና ሽፋን መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት። “ብዙኀን መገናኛ ተቋማት በሕዝቦች መካከል አንድነት ለመትከልና ሥር እንዲሰድ ለማድረግ የማይተካ ሚና አላቸው” ሲሉም ተናግረዋል አፈ ጉባዔው።
18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት «ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት» በሚል መሪ መልዕክት ሕዳር 29/2016 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ በሚካሄድ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በድምቀት ይከበራል፡፡
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		