“ለተሟላ ሰላም ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ ቢኾንም በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንጻራዊ ሰላም አምጥቷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

37

ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ4ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ እንደራሴዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በአማራ ክልል ስላለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትግበራ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋነኛ ዓላማው ሰላምና ደኅንነትን ማምጣት መኾኑን ገልጸዋል፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው የክልሉ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንጻራዊ ሰላም አምጥቷል፤ የክልሉን መንግሥት ከመፍረስ ታድጓል፤ ነገር ግን የተሟላ ሰላም እንዲመጣ ተጨማሪ ሥራ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ለሕዝባችን የገባነውን ቃል ለመፈጸም እንሠራለንም ብለዋል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲፋጠን እና ድህነት እንዲጠፋ ሕዝቡ ይፈልጋል፤ ዲሞክራሲ እንዲገነባ ይፈልጋል፤ ሕዝብ ማለት ቀጣይነት ነው፣ ለልጆቹ የተሻለ ነገን ያስባል ብለዋል፡፡

የሕዝብን ጥያቄ እናውቃለን፣ ለሕዝባችንም ቅርብ ነን፣ የሕዝቡን ፍላጎት እና ጥያቄ ለመመለስ በጋራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ለአንደኛው መልስ የሚኾነው ለሌላኛው ጥያቄ ስለሚኾን የሕዝብን ጥያቄ በስክነት እና በትክክል ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

መንግሥታቸው ድፍረት የሚያስፈልጋቸውን ጥያቄዎች በመድፈር መመለስ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡

በአማራና በትግራይ ክልል የሚገኙ አወዛጋቢ ሥፍራዎች ጉዳይ የመፍቻ ቁልፍ መንገድ ማበጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡

የተቀመጠው የመፍቻ መንገድ ላይ መወያየት ይገባል ነው ያሉት፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሕዝብን ያማካለ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ችግሮቻቸውን በጋራ እንፈታለን ካሉ በደስታ እንቀበላለንም ብለዋል፡፡

ችግሮችን በስክነት በማየት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ሁሉንም ማርካት አይቻልም፣ የእኛ መፍትሔ ብቸኛው ነው አንልም፣ መፍትሔ ያለው ሁሉ ያምጣ ፣ መፍትሔው ግን ሰላም የሚያመጣ መኾን ይገባል ነው ያሉት፡፡

ለችግሮች ሰበብ ማብዛት እንደማይገባም አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለኢትዮጵያውያን የምመክረው በጥይት ከመገዳደል፤ በሀሳብ መገዳደር ይሻላል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“ብዙኀን መገናኛ ተቋማት በሕዝቦች መካከል አንድነትን ለመትከልና ሥር እንዲሰድ ለማድረግ የማይተካ ሚና አላቸው” አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር