“ለኢትዮጵያውያን የምመክረው በጥይት ከመገዳደል፤ በሀሳብ መገዳደር ይሻላል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

41

ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭቶች መኖራቸው ገልጸዋል፡፡ በክልሎች ያለው ግጭት ሰው የሚገድሉ፣ ንብረት የሚያወድሙ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የእኛ መሻት ሰላም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን ድረስ በእኛ መሻት ጦርነት አልተካሄድም ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ግጭቶች እና ጦርነቶች የሚከሰቱት በሌሎች ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡

እኛ በቀደድነው ክፍተት ሌሎች ኃይሎች እንዳይገቡ ስለምንፈልግ እና ኢትዮጵያን ስለማናሳንሳት ጦርነት መክፈት አንፈልግም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሳናሳንሳት በጋራ ብንሠራባት ታላቅ ሀገር ናት ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ከመኖር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸውም አመላክተዋል፡፡ አሁን በሚደረጉ ግራና ቀኝ ባሉ ውጊያዎች መንግሥትን ማሸነፍ አይቻልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በሕልውናዋ የሚመጡባትን ልማቶቿን አዘግይታም ቢሆን ትታገላለች ነው ያሉት፡፡ለኢትዮጵያውያን የምመክረው በጥይት ከመገዳደል፣ በሀሳብ መገዳደር ይሻላል ብለዋል፡፡

ጥይት ዶላር መኾኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር በኢኮኖሚ የሚጎዳ፣ ሰው የሚገድልና ወደፊትም ቀና እንዳንል የሚያደርግ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ግጭትን እና ጦርነትን በመተው በውይይት ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ሀሳባችን የጥላቻ ግንብ አፍርሰን የይቅርታ ድልድይ እንገንባ ነው፣ የመገዳደሉን ሰይፍ እንተውም ብለዋል፡፡ ፍቅር፣ አብሮነት እና በጋራ ሰላምና ልማትን ማምጣት ይገባል ነው ያሉት፡፡
አንደኛውን የሕዝብ ተቆርቋሪ ሌላኛውን እንደማይቆረቆር መቁጠር አይገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ጠመንጃን ማውረድ እና ሃሳብ መንጃውን መያዝ የተሻለ ጥቅም እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

በማንኛውም ሰዓት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት ዝግጁ መኾናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሴራ አናምንም ብለዋል በምላሻቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከፖለቲካ ታሪኮች ባለፈ ሌሎች የጋራ ታሪኮችን ማጉላት ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“ለተሟላ ሰላም ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ ቢኾንም በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንጻራዊ ሰላም አምጥቷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)