
ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በምላሻቸውም ጥያቄዎችን ከሥረ መሠረቱ መገንዘብ እና መርመር ይገባል ብለዋል፡፡ ችገሮችን እኩል የሞንገነዘባቸው እና የሞንረዳቸው ከሆነ ጉዟችን ወደ መፍትሔ ይኾናል ነው ያሉት፡፡ በችግሮች ላይ መግባባት ካልቻልን ላይ መፍትሔ ላይ አንደርስም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የችግር ትንታኔ የስሜት እና የሤራ ትንታኔ እንደሚበዛውም ገልጸዋል፡፡ የሴራ እና የስሜት ትንታኔዎች ችግሩን እንዳንረዳ እና ከመፍትሔው እንድንርቅ ያደርገናልም ብለዋል፡፡
ብልጽግና የሚመራው መንግሥት የተለያዩ ስያሜዎች ይሰጡታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄ የኾነው የስሜትና የሤራ ትንታኔ በመኖራቸው ነው ብለዋል፡፡ ለየትኛውም ሴራ መጠቀሚያ እንደማይኾኑም አስታውቀዋል፡፡
የሤራና እና የስሜት ትንታኔዎች የጋራ ግንዛቤ እና መግባባት እንዳይኖር እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሁሉም ጫፍ ያሉ ልጆቿ በእኩልነት የሚኖሩባት፣ ሁሉም የሚከበሩባት፣ ያማረች ሀገር እንድትፈጠር እንሠራለንም ነው ያሉት፡፡
በመንግሥታቸው ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መፍጠር እና አካታች የዲሞክራሲ ሥርዓት መገንባት ትኩረት እንደተሰጠውም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መሠረት የእያንዳንዱ ዜጋ ድምር ውጤት ነውም ብለዋል፡፡ በጋራ የመበልጸግ እና የመኖር እምነት እንዳላቸውም አመላክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አካታችና ሁሉን ያቀፈ ፓርቲ ኖሮ እንደማያውቅም አንስተዋል፡፡
ከተለመዱ ነገሮች በመውጣት ሰላምን ማስቀደም፣ ችግሮችን መፍታት፣ ደህነትን ማስቀረት እና ሰላምን ማምጣት ይገባልም ብለዋል፡፡ የተሻለ ነገር ለማምጣት ሃሳብ ማመንጨት እና መተግበር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደኛው ችግር አባባሽ ትርክት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ነጠላ፣ የተዛባ እና አፍራሽ ትርክት ሀገር እንደማይገነባም ገልጸዋል፡፡ ታላቅ እና ሀገራዊ ትርክት ይሰበስባል፣ ከዚያ የሚቃረነው ሀገር ይበትናል፤ ስንለያይ አቅማችን ያንሳል እንጎዳለን ነው ያሉት፡፡
ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን ማስፋት ጎጂ መኾናቸውንም አንስዋል፡፡ ዋልታ ከረገጠ እሳቤ ሚዛን ወደሚደፋ እሳቤ መምጣት ይገባልም ብለዋል፡፡
አላካኪነት ሌላው ችግር እንደኾነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማላከክ ለውጥ አይመጣም፣ ለውጥ የሚመጣው ኀላፊነት በመውሰድ መኾኑን አንስዋል፡፡
በጊዜ መታከክ እና አቅላይነት ሌላው ችግር መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ማስተካከል ለሀገር አንድነት እንደሚጠቅምም ተናግረዋል፡፡ የጋራ የሆነ ነገር መፍጠር ካልቻልን ለልጆቻችን የሚተርፍ ችግር እናወርሳንም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!