
ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኩፍኝ በሽታን ለመቆጣጠር እየተሠራ ቢኾንም በየጊዜው በሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ፈተና እየኾኑ እንደኾነ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት የኩፍኝ ወረርሽኝን በአንድ አካባቢ ላይ እንዳይደርስ የክትባት ሽፋኑ ቢያንስ ከ90 በመቶ በላይ ተደራሽ መኾን ይገባዋል።
ይሁን እንጅ ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረው ክትባት በሰሜኑ ጦርነት እና በተለያዩ ምክንያቶች በመቋረጡ በበርካታ ወረዳዎች የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር። ወረርሽኙንም በመደበኛ እና በዘመቻ ክትባት መቆጣጠር ተችሎ እንደነበር ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
እንደገና በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር እና መሰል ምክንያቶች በክትባቱ ላይ ተጽዕኖ በማሳደሩ የኩፍኝ በሽታ ተከስቷል። ኢንስቲትዩቱ ከሌሎች ጤና ተቋማት ጋር በመቀናጀት አሁን ላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ሕክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
የሰላሙ ሁኔታ ከተመለሰ የክትባት ሽፋኑን በሁሉም ወረዳዎች ለማዳረስ እንደሚሠራም ነው ያስገነዘቡት። አሁን ላይ የኩፍኝ በሽታ ቅኝት ሥራም እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!