ሴቶችን በአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ በማሳተፍ እና በማበረታታት የተሻለ ነገን መፍጠር ይገባል ተባለ፡፡

55

አዲስ አበባ: ኅዳር 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሴቶች በአየር ንብረት ለውጥ ያላቸውን ተሳትፎ በመጨመር ያለው አስፈላጊነት በሚል ሃሳብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ ጋር በመተባበር የኮፕ 28 የአየር ንብረት ለውጥ የግማሽ ቀን ውይይት አካሂዷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ሴቶችን ስናበረታታ ሃብትን እና የዓለምን ኢኮኖሚ እያነቃቃን ነው ብለዋል። ሴቶችን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ስናበረታታ ለዓለም ትልቅ ጥቅም አለው ብለዋል፡፡

ሴቶች በአየር ንብረት ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ያላቸው ሚና ከፍ ያለ ነው፤ በመኾኑም ሴቶችን ደገፈን እና አበረታታን ማለት የአየር ንብረት ለውጥን ደገፍን ማለት ነው ብለዋል፡፡

ሴቶች የመልካም ነገር እና የለውጥ አቀጣጣይ ማድረግ ይቻላል ብለዋል። ለዚህ ማሳያው ኢትዮጵያ 32 ቢሊዮን ችግኝ ስትተክል ሴቶች በብዙ መልኩ ተሳታፊ ነበሩ። ሴቶችን ሥናበረታታ የአየር ንበረት ለውጥ ጫናን በሚገባ መልኩ መከላከል እና አቅም መፍጠር መቻል ማለት ነው፤ የነገ ትውልድ የተሻለ ገፅታ መገንባት ቻልን እንደማለት ይቆጠራል ብለዋል፡፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢምባሲ በኢትዮጵያ ምክትል አምባሳደር ሱኡድ አልታጂ በአየር ንበረት ለውጥ ሒደት ሀገራችን በኮፕ 28 ከፍተኛ ሚና እንዲኖራት ትሠራለች ብለዋል፡፡

ሴቶችን ማበረታታት የተመድ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት መቻል እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡ 70 በመቶ የዩኤኢ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሴቶች ናቸው፤ የመጀመሪያዋ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች አስትሮኖሚስትስ ሴት ነች ብለዋል ምክትል አምባሳደሩ።

50 በመቶ በሳይንስ እና ምርምር ዘርፍ የሚሠሩ የሀገሪቷ ሰዎች ሴቶች ናቸው ያሉት ምክትል አምባሳደሩ በማንኛው ዘርፍ ሴቶችን በማሳተፍ ሥራዎች መሥራት ተገቢ ነው ብለዋል። ይህ የሚያሳየው ሴቶችን ማጠናከር ለሀገር ምን ያክል አሥፈላጊ መኾኑን ነው ብለዋል።

የተሻለ ነገን እና የምትመች ዓለም ለመፍጠር የሴቶችን አቅም መጠቀም፣ ማሥተባበር እና ነገን ብሩህ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አንስተዋል።

ዘጋቢ፡- አንዷለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እንጅባራ በሰላም ወዳድ ነዋሪዎቿ ሰላሟ ይጠበቃል” ነዋሪዎች
Next article“የተከሰተው የጸጥታ ችግር የወረርሸኝ በሽታዎችን ለመከታተል እንቅፉት ኾኗል” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት