
ደብረ ብርሃን: ሕዳር 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመኸር ወቅት የታጣውን ምርት በመስኖ ለማካካስ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሰሎሞን ቀለሙ በዞኑ በ2015/16 የምርት ዘመን ከ490 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በሰብል ተሸፍኗል። ከዚህ ውስጥ165 ሺህ ሄክታሩ በገበያ ተኮር ምርቶች የተሸፈነ ነው።
በዞኑ በተያዘው የምርት ዘመን በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች 65 ሺህ152 ሄክታር ሰብል ከምርት ውጭ መኾኑ ተጠቅሷል። የግብዓት አቅርቦት፣ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ፣ ተባይ እና በሽታ በምክንያትነት ከተቀመጡት መካከል ናቸው።
ይህንን ምርት በመስኖ ለማካካስ ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ መጠነ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ስለመኾኑም አቶ ሰሎሞን ተናግረዋል።
በዞኑ 73 ሺህ ሄክታር ማሳ በስንዴ ሰብል መሸፈኑንም ምክትል ኀላፊው በአንጎለላና ጠራ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የስንዴ ሰብል በጎበኙበት ወቅት ተናግረዋል።
የአንጎለላና ጠራ ወረዳ የግብርና ኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ ስንታየሁ ግዛቸው ወረዳው በምርት ዘመኑ ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ በሰብል የተሸፈነ ሲኾን 404 ሄክታሩ በኩታ ገጠም የለማ ስንዴ መኾኑን ገልጸዋል።
በኩታ ገጠም ያለሙት የስንዴ ሰብል በተሻለ ቁመና ላይ በመኾኑ ምርታማ እንደሚኾኑም አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ ደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር እና ሌሎች በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚሠሩ ተቋማት ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ሰፊ ሥራ እያከናወኑ እንደኾነም ተገልጿል።
ዘጋቢ:- ገንዘብ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!