
ባሕር ዳር: ኅዳር 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት ለተደራጁ ማኅበራት እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ርክክብ ጀምሯል።
በልማት ተነሺነት ትክ ቦታ እንዲሠጣቸው ካመለከቱት የአርሶ አደር ቤተሰቦች መካከል 600 እና በማኅበር ከተደራጁ ቦታ ጠያቂዎች መካከልም 800 ያክሉ መሥፈርቱን ስለማያሟሉ መታገዳቸው ተገልጿል። በዚህም 92 ሄክታር መሬት ከዘረፋ መዳኑ ተጠቅሷል።
የባሕር ዳር አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው አሁን ላይ የተደራጁትን ማኅበራት ቦታ ሰጥተን ለመጨረስ እየሠራን ነው ብለዋል።
”ሕዝቡ በቤት ሥራ ማኅበር እናደራጃለን በማለት ገንዘብ ከሚሰበስቡ ደላሎች እንዲጠነቀቅ” አሳስበዋል። በዚህ ሕገ ወጥ ሥራ በተሠማሩት ሰዎች ላይም እርምጃ መወሰድ መጀመሩን ገልጸዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ አሁን ላይ ለቤት ሥራ ማኅበር ምንም ዓይነት የማደራጀት ሥራ እየሠራ አለመኾኑን እና ማደራጀት ሲጀምር በማስታወቂያ ይፋ እንደሚያደርግ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!