የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በመኖሪያ ቤት ቦታ ለተደራጁ ማኅበራት እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ርክክብ አደረገ።

130

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ በ1 ሺህ 2 መቶ የቤት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት ለተደራጁ ማኅበራት እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ርክክብ አድርጓል።

በዛሬው እለት በተከናወነው መርሐ ግብር የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የተሠጣቸው ለአንድ መቶ አርሶ አደሮች እና ለአንድ መቶ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መኾኑን፤ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ተሻገር አዳሙ ገልጸዋል።

የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ካገኙት የቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መካከል የቡራቀን እና የብኖር አየሁ ማኅበራት ይገኙበታል። የማኅበራቱ አመራሮች አቶ የሸዋስ ክብረት እና አቶ ግርማ ይስማው በሠጡት አሥተያየት ኅብረተሰቡ ለበርካታ ዓመታት ተደራጅቶ በቦታ ጥያቄ መቆየቱን ገልጸዋል። አሁን ላይ ያ ሁሉ ችግር አልፎ ወደ ይዞታ ማረጋገጫ ርክክብ መደረሱ እንዳሥደሰታቸውም ተናግረዋል። ለሌሎች ማኅበራትም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እና የግንባታ ፈቃድ በፍጥነት እንዲሠጥ ጠይቀዋል።

የዘንዘልማ አካባቢ ነዋሪ አርሶ አደር ቄስ ተፈራ ደሴ በበኩላቸው ለቤት ልማቱ በተወሰደባቸው የአትክልት መሬት ትክ አምስት መቶ ካሬ ሜትር የቤት መሥሪያ ቦታ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። በቅርቡም ግንባታ ጀምረው ለልጅ ልጅ የሚሆን ጥሪት እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የተጀመሩትን እያጠናቀቅን እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እየሠራን ሕዝብን ተጠቃሚ እናደርጋለን ብለዋል።

”የመሥሪያ ቦታ ያገኛችሁ ሙሉ ጊዜያችሁን ቤት በመገንባት ላይ እንጂ አልባሌ ቦታ እንደማናገኛችሁ ተስፋ እናደርጋለን” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሰላም ያሥፈልጋልና ለሰላም ትኩረት መሥጠት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በባሕር ዳር ከተማ ከ28 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በ1 ሺህ 2 መቶ የቤት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት እየተጠባበቁ ነው።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ቤት በመገንባት ላይ እንጂ በአልባሌ ቦታ ላይ እንደማናገኛችሁ ተስፋ እናደርጋለን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next article“በተቀደሱት ቅርሶች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም” የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር