”ቤት በመገንባት ላይ እንጂ በአልባሌ ቦታ ላይ እንደማናገኛችሁ ተስፋ እናደርጋለን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

63

ባሕር ዳር: ሕዳር 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት ለተደራጁ ማኅበራት እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ርክክብ አድርጓል።

የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የተሰጠው ለአንድ መቶ አርሶ አደሮች እና ለአንድ መቶ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ተሻገር አዳሙ ገልጸዋል።

የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ካገኙት የቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መካከል የቡራቀን እና የብኖር አየሁ ማኅበራት ይገኙበታል። የማኅበራቱ አመራሮች አቶ የሸዋስ ክብረት እና አቶ ግርማ ይስማው በሰጡት አስተያየት ኅብረተሰቡ ለበርካታ ዓመታት ተደራጅቶ በቦታ ጥያቄ መቆየቱን ገልጸዋል። አሁን ላይ ያ ሁሉ ችግር አልፎ ወደ ይዞታ ማረጋገጫ ርክክብ መደረሱ እንዳሥደሰታቸውም ተናግረዋል። ለሌሎች ማኅበራትም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እና የግንባታ ፈቃድ በፍጥነት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የዘንዘልማ አካባቢ ነዋሪው አርሶ አደር ቄስ ተፈራ ደሴ ለቤት ልማቱ በለቀቁት የአትክልት መሬት ትክ አምስት መቶ ካሬ ሜትር የቤት መሥሪያ ቦታ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። በቅርቡም ግንባታ ጀምረው ለልጅ ልጅ የሚኾን ጥሪት እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የተጀመሩትን እያጠናቀቅን እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እየሠራን ሕዝብን ተጠቃሚ እናደርጋለን ብለዋል።

”የመሥሪያ ቦታ ያገኛችሁ ሙሉ ጊዜያችሁን ቤት በመገንባት ላይ እንጂ አልባሌ ቦታ እንደማናገኛችሁ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም ተናግረዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሰላም ያስፈልጋልና ለሰላም ትኩረት መሥጠት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኑሮ ውድነት ለማስተካከል ሰላምን በማስፈን ነጻ የምርት ዝውውር መፍጠር እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
Next articleየባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በመኖሪያ ቤት ቦታ ለተደራጁ ማኅበራት እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ርክክብ አደረገ።