
ባሕር ዳር: ሕዳር 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማስተካከል በክልሉ ሰላምን ማስፈን እና ነጻ የምርት ዝውውር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል። በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ጥረት ማድረግ እንዳለበት የቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ ገልጸዋል።
አቶ ፈንታው በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የኑሮ ውድነቱን የመቀነስ ሥራን ማስተጓጎሉን ተናግረዋል። ይህም በዓለም ላይ ከተከሰተው የሸቀጦች ዋጋ መናር ጋር ተጨማምሮ የኑሮ ውድነቱ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መኾኑን አንስተዋል፡፡
አማራ ክልል የሀገሪቱን 40 በመቶ ምርት የሚሸፍን ቢሆንም ምርቱ ከሚመረትበት ቀበሌ እና ወረዳ ወደ ትላልቅ ከተሞች ነጻ የምርት ዝውውር ባለመኖሩ የኑሮ ውድነቱ አርሶ አደሩን ጨምሮ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍልችን እየፈተነ ይገኛል ብለዋል፡፡
የሰላም መደፍረስ በንግድ ሥርዓቱ ላይ ብልሹ አሠራሮች እንዲፈጠሩ አድርጓል፤ ሕገ-ወጥ ኬላ እና ቀረጥ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በየቦታው የተፈጠሩ ሕገ-ወጥ ኬላዎች በምርት አቅርቦትና ግብይት ላይ ችግሮች እንዲከሰቱ እያደረጉ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
የኑሮ ውድነቱ አሁን ካለበት የባሰ እንዳይኾን በክልሉ ዘላቂ ሰላም ማስፈን፣ የግብርና ምርቶችን ማሳደግ እና ነጻ የኾነ የምርት ዝውውር ሥርዓትን በማስፈን ረገድ ሁሉም ባለድርሻ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!