18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ከሕዳር 25 ጀምሮ በጅግጅጋ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

622

አዲስ አበባ: ኅዳር 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ብዝኃነት እና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በዓሉ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናግረዋል።

ላለፉት 17 ዓመታት በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች በልዩ ልዩ መሪ መልዕክቶች ሲከበር መቆየቱን አፈ ጉባኤው አስታውሰው በእነዚህ ዓመታት በዓሉ እንዲከበር ከተወሠነባቸው ዓላማዎች አንፃር ብዙ ጥቅሞች ተገኝተውበታል ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የበዓሉን አከባበር አሥመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡

አፈ ጉባኤ አገኘሁ በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ልምዳቸውን፣ ተሞክሯቸውን እና ባህላቸውን የሚለዋወጡበት፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ ለዘላቂ ሰላምና ለፈጣን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት የሚነሳሱበት በዓል መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

አፈ ጉባኤው አያይዘውም ባለፉት 17 ዓመታት በዓሉ ሲከበር ሕዝቦች ለረዥም ዘመናት ይዘውት የቆዩትን አብሮነት እንዲያፀኑ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነት እንዲያጎለብቱ እና በሕገ መንግሥቱ እና በፌዴራል ሥርዓቱ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲፈጠሩ የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች እንደተሠሩ እና በነዚህም ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አሥረድተዋል።

18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሥተባባሪነት በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት «ብዝኃነት እና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት» በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይቶች፣ በጎዳና ላይ ትዕይንቶችና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት ይከበራል ብለዋል አቶ አገኘሁ፡፡

የዘንድሮው በዓል ሲከበር ብዝኃነትን በማስተናገድ እና ሕብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያን በማጠናከር ሀገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት ተሠጥቶት እንደሚከናወን አሥታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ አንድነትን የሚያስጠብቁ አንኳር ተግባራት ቅድሚያ የሚሠጣቸው ሲኾን በተለይም ለሀገር ሕልውና መከበር ሲባል አማራጭ የሰላም መንገዶችን ሁሉ መጠቀም ለምርጫ የማይቀርብ ተደርጎ እንደሚሠራ አስገንዝበዋል፡፡

በዓሉ ከኅዳር 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ በፌደራልና የክልል ተቋማት በተለያዩ ኹነቶች የሚከበር ይኾናል ያሉት አቶ አገኘሁ ዋናው በዓል በጅግጅጋ ከተማ ከኅዳር 25/2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አምስት ተከታታይ ቀናት የሚከበር ይሆናል ብለዋል።

አምስቱ ቀናትም የተለያዩ ስያሜዎች የተሰጣቸው ሲኾን ኅዳር 25 የወንድማማችነት ቀን፣ ኅዳር 26 የብዝኀነት ቀን፣ ኅዳር 27 የአብሮነት ቀን፣ ኅዳር 28 የመደመር ቀን፣ ኅዳር 29 ደግሞ የኢትዮጵያ ቀን በሚል ስያሜ ይከበራሉ ብለዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን የሚሳተፉበት ለ10 ቀናት ያህል የሚቆይ የሶማሌ ክልል ምን እንደሚመስልና ኅብረ ብሔራዊነቱን የሚዳስሱ ዘገባዎችን የሚሠሩበት ጉብኝትም ከህዳር 5/2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ አፈ ጉባኤው አሥታውቀዋል።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ ኅዳር 03/2016 ዓ.ም ዕትም
Next articleምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ያካሂዳል ።