
ባሕር ዳር: ሕዳር 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የኾኑት ጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻ ኢትዮጵያን ይበልጥ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ገቢው እንዲያድግ ያየደርጋሉ ሲል የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ገልጿል።
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ፍጹም ገዛኸኝ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙት የጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻ ፕሮጀክቶች ለሀገራችን ተጨማሪ የቱሪስት መስህቦችን በመፍጠር ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ ፋይዳ ያበረክታሉ ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ በአዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በውጭ ምንዛሪ ግኝት ያላቸው አስተዋፅዖ የጎላ መኾኑን ገልጸዋል። የጎብኚዎች የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም በማድረግ በጎ ሚና እንደሚኖራቸው አንስተዋል።
ከዚህ ቀደም ጎርጎራን ለመጎብኘት የሚሄዱ ጎብኚዎች ጎንደር አንድ ተጨማሪ ምሽት አርፈው ይሄዱ እንደነበረ ያነሱት አቶ ፍጹም፤ አሁን ላይ ጎርጎራ ራሱን የቻለ ደረጃውን የጠበቀ ማረፊያ እና መዝናኛ ስፍራ ስለኾነ ጎብኚዎች ሁለት እና ሦስት ቀናት ተዝናንተው ወደ ጎንደር እና ሌሎች እንዲያቀኑ ዕድል ይፈጠራል ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹ ከሀገር አቀፍ የቱሪዝም ገቢ ባለፈ ለየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ ናቸው ብለዋል አቶ ፍጹም። በመዳረሻዎቹ ለተገነቡ ሆቴሎች፣ በትራንስፖርት እና በአስጎብኚ ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥሩም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ፍጹም ገለጻ፤ አዳዲስ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት እየተገነቡ የሚገኙ መዳረሻዎች የዘርፉን ዕድገት በማፋጠን የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብት በአግባቡ ለመሸጥ አይነተኛ መንገድ ናቸው።
ለምረቃ ዝግጁ የኾኑትን ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ሲገቡ አስጎብኚ ማኅበራት በይበልጥ በማስተዋወቅ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ወደ ፕሮጀክቶቹ የሚያቀኑ ጎብኚዎች በየስፍራዎቹ ረዘም ላሉ ቀናት የሚቆዩባቸው መሠረተ ልማቶች ስለተሟሉ ከዘርፉ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የሚቻልበት ዕድል እንደተመቻቸ አስረድተዋል።
ጎብኚዎች ከፕሮጀክቶቹ በተጓዳኝነት ከዚህ ቀደም የሚጎበኙ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ስፍራዎች የሚጎበኙበት አጋጣሚ ስላለ የቆይታ ጊዜን ከማራዘም አንጻር እንደሀገር ተጠቃሚ መኾን ይቻላል ያሉት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፤ አሁን ላይ ጎብኚዎች እንዳይመጡ እንቅፋት እየኾነ ያለው የሰላም እጦት ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ ላይ ያለው የሰላም እጦት ለቱሪዝም ዘርፉ ማነቆ በመኾኑ ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የየአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ማሳደግ እንዳለበት ተናግረዋል።
የቱሪስት መስህቦች በሚገኙባቸው አካባቢዎች እንደ መንገድ፣ መብራት፣ የስልክ ኔትወርክ፣ የማረፊያ ቦታዎች እጥረት እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ማሟላት ተገቢ መኾኑንም አንስተዋል።
ኢፕድ እንደዘገበው ሀገሪቷ ያላትን የቱሪዝም አቅም የበለጠ ለመጠቀም እና ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ በጋራ መሥራትን እንደመፍትሄ አንስተዋል አቶ ፍጹም።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
