
ባሕር ዳር: ኅዳር 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የማይረሱ በደሎች ደረሱባት፤ ለጀሮ የሚከብዱ ግፎች ተፈጸሙባት፤ ንጹሐን ያለ ጥላ እና ከለላ ተሰቃዩባት፤ ማንነታቸው እየተለዬ የመከራ ጽዋ ተጎነጩባት፤ እንደ ቅጠል ረገፉባት፤ አንጀት የሚያንሰፈስፍ የመከራ ድምጽ አሰሙባት፤ ደማቸውን አፈሰሱባት፤ አጥንታቸውን ከሰከሱባት፡፡
በዚያች ምድር የማይረሱ ቀኖች፤ የማይዘነጉ ግፎች፤ ዓመታት አልፈው ዓመታት በተተኩ ቁጥር የሚታወሱ በደሎች ሞልተው ፈስሰውባታል፡፡ ንጹሐን በቀል ባሰከራቸው ምስለ ሰዎች ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ከእርስታቸው አፈናቅለዋቸው፣ ያለ ማንነት ማንነት ጭነውባቸው፣ ያለ ቋንቋቸው ሌላ ቋንቋ በግድ አናግረዋቸው፣ ያለ ማንነታቸው ሌላ ማንነት ሰጥተዋቸው፣ በታሪካቸው አድርገውት የማያውቁትን ሁሉ አድርገዋቸው አልበቃ ሲላቸው በጅምላ እየገደሉ በጅምላ ጣሏቸው፤ ለተወለዱባት አፈር እንዳይበቁ ከለከሏቸው፡፡ አስከሬን በሚከበርበት ሀገር በጅምላ ለአራዊት ሰጧቸው፡፡ የመከራና የስቃይ ዶፍ አወረዱባቸው፡፡
እኒያ ከገጀራ የተረፉ ነፍሶች እንኳን የዛን ጊዜ ዛሬ ላይ ኾነው እንኳን ሲያስታውሱት፣ ሲያስቡት እና ሲያንሰላስሉት ይሰቀጥጣቸዋል፡፡ የሚኾኑትን ያሳጣቸዋል፡፡ ስለምን ቢሉ ሺህዎች አንገታቸውን ሲቀሉ ተመልክተዋል፤ ሺህዎች ነብሳቸው ከስጋቸው አልለይ ብላ ሲማቅቁ አይተዋል፡፡ በጣዕረሞት ውስጥ ኾነው የመከራ ሌሊት ሲያሳልፉ ሰምተዋል፡፡ አባቶቻቸው ለዓይን እና ለጆሮ የሚከብድ ግፍ ሲፈጸምባቸው እየተመለከቱ በድንጋጤ እየተንቀጠቀጡ የሚያነቡ ሕጻናትን አስተውለዋልና፡፡
በማይካድራ የደረሱትን ግፎች የትኛው አንደበት ነግሮ ይጨርሳል፡፡ የትኛው ብዕርስ በትክክለኛው ይገልጻል፡፡ የትኛው ወረቀትስ ከጭካኔ ሁሉ የከፋውን ጭካኔ፣ ከግፍ ሁሉ የከፋውን ግፍ ይመዘግባል፡፡ የደረሰው ግፍ እና ጭካኔ የከፋ ነውና ከኾነው ሁሉ ጥቂቱን መናገር ይቻላል እንጂ ሁሉንማ እንዴት መግለጽ ይቻላል ይላሉ እኒያ ከሞት የተረፉ ነፍሶች፡፡
ብዙ ነገር ይዘነጋል፣ በማይካድራ የኾነብንን ግን አንረሳውም ይሏታል፡፡ እንኳን እነርሱ ያዩዋት ታሪኳን የሚሰሟት ልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸውም በወላጆቻቸው ላይ የተፈጸመውን አይረሱትም፤ እንዳስታወሱት፣ እንዳሰቡት እና እንደዘከሩት ይኖራሉ እንጂ፡፡
የሺ ላቀ ይባላሉ፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት ከማይካድራ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የተረፉ እናት ናቸው፡፡ የሁለት ልጆች እናትም ናቸው፡፡ የልጆቻውን አባት ዓይናቸው እያዬ በግፍ ተነጥቀዋል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የኾነው እንደ ዛሬ፣ ከዛሬም እንደ አሁን፣ ከአሁንም እየተደረገ እንዳለ ቅጽፈት ያዩታል፡፡ ያ መጠን የሌለው ግፍ አይወጣላቸውም፤ ያ ልክ የሌለው በደል አይረሳቸውምና፡፡ በደሉ፣ መሳደዱ፣ መገፋቱ እና መዳፋቱ ለዓመታት የዘለቀ ነበር፡፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ክህደት ፈጽመው ጦርነት ከጀመሩ ጀምሮ የነበረው ግን ከሁልጊዜም የባሰ፣ መከራና ስቃይ የበዛበት ነበር ይላሉ ወይዘሮ የሺ ያን ጊዜ ሲያስታውሱት፡፡
የሺ ጥቅምት 30 እና ከዚያ ቀጥሎ ያሉትን የመከራ ቀናት ሲያስታውሷቸው እንባ ይቀድማቸዋል፡፡ ስለዚያ ጊዜ ሲናገሩም በእንባ እየታጠቡ ሳግ እየተናነቃቸው ነው፡፡ “እጅግ በጣም አሰቃቂ ነው፤ እስካሁን ድረስ ከልባችን ላይ ጥቁር አሻራ እንደተጻፈ ነው፤ በአማራነታችን ብቻ ግፍና በደል ተፈጽሞብናል፤ የዘር ማጥፋት ወንጀል በእኛ ላይ ተፈጽሟል፡፡ ግድያው እጅግ አሰቃቂ ነበር፤ አገዳደላቸው በገጀራ ነው” ነው ያሉት ጊዜውን ሲያስታውሱ እንባ እየተናነቃቸው፡፡
የሺ ሠርተው የሚበሉ፣ ከዛሬ ነገ የተሻለን ኑሮ የሚናፍቁ፣ ልጆቻቸውን በፍቅር ለማሳደግ የሚታትሩ፣ የእርሳቸው አንድ አካል አንድ አምሳላቸውን ነው የገደሉባቸው፡፡ ሚስት ከፊቷ ላይ ባሏ ሲሾም፣ ሲሸለም፣ ስሙ በመልካም ነገር ሲነሳ አብዝቶ ደስ ይላታል፡፡ ከእርሱ የበለጠ እርሷ ትኮራለች፡፡ አብዝታም ትደሰታለች፡፡ ባሏን ከፊቷ እንኳን ሲገድሉት በአልተገባ አተያይ ሲያዩትም አብዝቶ ይከፋታል፡፡ አብዝቶም ይቆጫታል፡፡ የሺ የሚያንገበግባቸው፣ የእግር እሳት ኾኖ የማይወጣላቸው፣ የልጆቻቸው አባት ከፊታቸው ላይ ሲገደሉ በመመልከታቸው ነው፡፡
“ባሌ ሠርቶ የሚበላ፣ ሠርቶ የሚያድር ነው፡፡ ከምንም ነገር የለበትም፡፡ ባሌ በአማራነቱ ብቻ ነው በግፍ የተገደለው፡፡ ኑሮውን ለመምራት የሚታገል እንጂ ከሌላ ውስጥ ምንም የለበትም፡፡ ከቤት ውስጥ ነው አውጥተው ከእኔ እና ከልጆቼ ፊት ባለቤቴን ሕይወቱን የነጠቁኝ፡፡ ታላቋ ልጄ የአሥር ዓመት ልጅ ናት፡፡ አባቷን በግፍ ሕይወቱን ሊነጥቁት ሲሉ እባካችሁ እያለች ለመነቻቸው፤ እነርሱ ግን ወንዶችን እንጨርስና እናንተን ደግሞ ነገ እንጨርሳችኋለን፤ ቀናችሁን ጠብቁ እያሉ ገደሉት፡፡ ለእኛም ለመሞት ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቶን ነበር፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ሃሳባቸው አልተሳካም፤ እኛ ተርፈናል” ነው ያሉን ያን ጊዜ በሳግ እያስታወሱ፡፡
ወይዘሮ የሺ ባለቤታቸውን ከፊታቸው ላይ በግፈኞች ተነጠቁ ፡፡ ልጆቻቸው እና እርሳቸው ሰማይ ተደፋባቸው፡፡ አይዟችሁ የሚል አጽናኝ አልነበረም፡፡ ይባስ ብሎ የሞት ሰይፍ እየዞራቸው፣ አሁን አሁን መጣሁ እያለ እያንዣበባቸው ነበር፡፡ “ እኛም መኖራችን እና መትረፋችን ይገርመኛል፡፡ ያደርነው ከሬሳ መካከል ነው” ነው ያሉን፡፡
ወይዘሮ የሺ እንደነገሩን ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም የተጨፈጨፉት ንፁሐን እስከ ሕዳር 3/2013 ዓ.ም ድረስ ሰብስቦ መጨረስ አልተቻለም ነበር፡፡ እንዳያልፍ የለም ያን ጊዜ አሳለፉት፤ እኒያን የመከራ ቀናት እድሜ አግኝተው ተረኳቸው፤ ለሰው ነገሯቸው፡፡ ለታሪክ አስቀመጧቸው፡፡ እውነትን ለሚሻ ሁሉ ገለጧቸው፡፡ ከተገፉት ለሚቆም ሁሉ ሕያው ምስክር ኾኑ፡፡ በየሺ ቤት ጥቁሩ ጠባሳ ባይለቅም፤ የሚወዱት፣ የሚወዳቸው፣ የልጆቻቸው አባት፣ አንድ አካል አንድ አምሳላቸው ቀና ብለው ባያዩም ከመከራ በኋላ ነጻነትን አይተዋል፤ በማንነት መኩራትን አግኝተዋል፡፡
“እንዳያልፍ የለም አለፈ፤ አሁን ተመሥገን ነው በራሳችን ቋንቋ ነው የምንናገረው፤ በፊት የራሳችን ቋንቋ ልንናገር እንሸማቀቅ ነበር፡፡ ለመኖር ስለ ምንፈልግ አማርኛ ለማውራት እንሰጋ ነበር፤ ስብሰባ እንኳን ለራሳቸው ጉዳይ ካልፈለጉን በስተቀር አይጠሩንም ነበር፤ እንደ ሰው አያዩንም፤ አሁን በራሳችን ቋንቋ ተነጋግረን፤ በአንድነት እየኖርን ነው፤ የሞተው ሞቶ መሥዋዕት ተከፍሎ የተመሠገነ ይሁን ነጻነት መጥቷል” ብለውናል ወይዘሮ የሺ የቀደመውን እና የአሁኑን እያነጻጸሩ ሲነግሩን፡፡
እኒያ በማይካድራ አማራዎች ላይ ግፍ የፈጸሙት ግን እንዲሁ ዝም ብለው መቅረት የለባቸውም፤ ተበዳይን የሚክስ፣ በዳይን የሚያስተምር ቅጣት ያስፈልጋልም ብለውናል፡፡ “ጥቅምት 30 እንኳን የተጎዳነው እኛ ይቅርና ሌላው ሰው አይረሳትም፤ ልጆቻችንን ይዘን እንዘክራታለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን እየሄድን እናስባቸዋለን” ነው ያሉን፡፡ የከተማ አሥተዳደሩ እና የዞኑ መሪዎችም ቀኗን በቁጭት እንደሚያከብሯት እና እንደሚዘክሯትም ወይዘሮ የሺ ነግረውናል፡፡
ከመከራ ቀኖች ከማይረሱ በደሎች ውስጥ ተርፈው የተገኙት ታደሰ አዲስም የተፈጸመውን ባሰቡት ቁጥር የከፋ ስሜት እንደሚሰማቸው ነግረውናል፡፡ “ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም የደረሰውን ግፍ እና መከራ ይህ ነው ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡ ሰው እንደ እንስሳት በሰው ሕይወቱ በግፍ እየተነጠቀ ሲጣል አየን” ይላሉ ያን ጊዜ ሲያስታውሱ፡፡
ታደሰ ከ30 በላይ ጓደኞቻቸውን እና ወዳጆቻቸውን በግፍ እንዳጡም ነግረውናል፡፡ የቀን ሥራ ሠርተው የሚኖሩ፣ ነገ ያልፍልናል የሚሉት ጓደኞቼ አለቁ ነው ያሉን፡፡ ያን ጊዜ ሲያስታውሱ በጓደኞቼ ላይ የኾነውን ሁሉ ሳይ የምኾነውን አጣሁ፡፡ በደመነብስ ለማምለጥ ሞከርኩ፡፡ ወደ ቤት ገብቼ ቤት ቆለፍኩ፡፡ እኔን ትረፍ ሲለኝ ከጎረቤት የሚያመልጣቸው ሰው ነበር ያን ሲያሳድዱ ሲሄዱ እኔ ቀረሁ” ይላሉ፡፡
በዚያች ሌሊት ንጹሐን እየተፈለጉ በለው፣ ያዘው እየተባሉ ተጨፈጨፉ፡፡ የመከራው ጽዋ የደረሳቸው በግፍ አለቁ፡፡ እድሜ የተጨመረላቸው እና ያን የመከራ ጊዜ ለመተረክ የተመረጡ በሰቀቀን ውስጥ፣ ከአስከሬን መካከል ተውጠው ተረፉ፡፡ “ያቺ ቀን የማትረሳና ዘግናኝ ናት፡፡ ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ለእኛ መቼም የማትረሳ ናት” ይሏታል፡፡
በማይካድራ ያለቁት ሁሉ አንድም በደለኛ የለም፤ ሁሉም ሠርቶ የሚበላ፤ የማንንም መብት የማይነካ እንደነበርም ነግረውናል፡፡ ሰዎችን እየገደሉ፣ ንብረታቸውን እየዘረፉ የግፍ ግፍ ፈጸሙ፡፡ ጣት እየቆረጡ የወርቅ ቀለበት ወሰዱ፤ እኛ የተሰቃየነው አማራዎች ስለኾንን እንጂ ወንጀለኞች ስለኾንን አይደለም፡፡ አማራ ካልጠፋ እኛ መኖር አንችልም በሚል ነው የጨፈጨፉት ነው ያሉት፡፡
“በግፍ ንጹሓንን ሲገድሉ አደሩ፡፡ ሲነጋ ሬሳውን በትራክተር ይጭኑ ነበር፡፡ የሞቱትን እጅ እና እግራቸውን እየያዙ ወደ ትራክተር ይወረውሯቸዋል፡፡ ወያኔ በእኛ ላይ የፈጸመው ግፍ ለዘለዓለም የሚረሳ አይደለም፡፡ በአማራ ላይ የተፈጸመው ግፍ እና መከራ አይረሳም፡፡ ሠርተው የሚበሉ ሌላ የማያውቁ ወንድሞቼን ነው የገደሏቸው፡” ነው ያሉን ያቺን የከፋች እና በበደል የተመላች ጊዜ እያስታወሱ ሲነግሩን፡፡
ቀኗ መቼ እንደኾነች አላወቁም እንጂ አስቀድመው ገና እናጠፋችኋለን፣ እንገድላችኋለን እያሉ ይዝቱባቸው እንደነበርም ነግረውናል፡፡ እንደ አቀዱት እና እንደ ፎከሩትም ጨፍጭፈውን ሄዱ፡፡ የማይረሳ በደል፤ የማይረሳ ግፍ ነውም ብለውናል፡፡ አሁን ያ ጊዜ አልፏል፡፡ ማነው ከእኛ በላይ ሲሉ የነበሩት ሁሉ ብን ብለው ጠፍተዋል፡፡ እኒያ በመከራ ውስጥ ያለፉት ንጹሐንም ከሞት መንጋጋ ወጥተው፣ በነጻነት መኖር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
አቶ ታደሰ የቀደመውን እና የአሁኑን እያነጻጸሩ ሲነግሩን “ አሁንማ ክብሩ ይስፋ፤ የሞቱት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እግዚአብሔር ነብሳቸውን በአጸደ ገነት ያስቀምጥልን እንጂ በመሥዋዕትነታቸው በአማርኛ አውርተን፣ በራሳችን ወንድሞች እየተመራን እንኖራለን፡፡ በወንድሞቻችን ደም ማንነታችንን አስመልሰናል፡፡
ያሳለፍነው መከራ የከፋ ነበር፡፡ አሁን በነጻነት እንኖራለን፡፡ የሞትንለት፣ የተሰደድንለት፣ ባሕላችን፣ ማንነታችን በእጃችን ነው፡፡ ነጻነትን ከማጣት ሕይወትን ማጣት የተሻለ ነው” ብለውናል፡፡
ማይካድራ ላይ እንደተፈጸመው ግፍ የተበደሉት ካሳ አልተካሱም፡፡ በዳዮችም አልካሱም፡፡ የበደላቸውን ልክ ቅጣት አላገኙም፡፡ ይህ ደግሞ ብዙዎችን ያስቆጫል፡፡ ያም ኾኖ ግን በነጻነት በመኖራቸው ደስተኞች ናቸው፡፡ “ፍትሕ ያልነው በነጻነት መኖራችንን፣ በነጻነት ሠርተን መግባታችንን፣ ከስድብ መውጣታችንን፣ ትጠፋላችሁ ሲሉን የነበረው ቀርቶ በነጻነት በመጫወታችን፣ ከዘመዶቻችን ጋር መገናኘታችን ለእኛ ትልቅ ደስታ ነው፡፡ ከትናንት ሰቆቃ እና መከራ ዛሬ ላይ ነጻ ወጥተናል፡፡ ይህ በጣም አስደስቶናል” ነው ያሉን፡፡
የወልቃይትን እውነት ማንም ያውቃል፡፡ አይደለም የሟች ወገኖች ገዳዮች ወልቃይት የእነርሱ እንዳልኾነ፣ በግፍ ይዘውት እንደነበር፡፡ የእነርሱ ኾኖ እንደማያውቅ ልባቸው ያውቃል፡፡ መገዳደል እንዳይኖር የወልቃይትን እውነት ማክበር እና መቀበል ይገባልም ብለውናል፡፡ ማንነታችንም በሕጋዊ መንገድ መከበር ይገባዋል፤ ማንነትን ከመነጠቅ ራስን ማጣት እና ሕይዎትን መነጠቅ ይሻላልና ነው ያሉት፡፡
“ወረራና መዋቅራዊ ዘር ማጥፋት በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት” በሚል ርእስ ለንባብ የበቃው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተጠናው የጥናት መጽሐፍ “የማይካድራ የዘር ጭፍጨፋ ሕወሓት በአደባባይ እና በግልጽ ከፈጸማቸው የዘር ጭፍጨፋዎች አንዱ ነው፡፡ ማይካድራ ላይ አማራዎች በአብዛኛው ድምጽ አልባ በኾነ መሳሪያ በዘራቸው ብቻ ተመርጠው ተጨፍጭፈዋል” ይላል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተጠናው ጥናት እንደሚገልጸው ጭፍጨፋው ታቅዶበት የተደረገ ነው፡፡ “የማይካድራ ጭፍጨፋ ፖለቲከኞች፣ የጸጥታ ኀላፊዎች እና የደኅንነት ሰዎች አቅደው፣ በጀት አዘጋጅተው፣ አሠልጥነው፣ ስምሪት ሰጥተው፣ መኪና አዘጋጅተው እና ዝርዝር መረጃ ይዘው በተጠና መንገድ የፈጸሙት ሲኾን የሕወሓት ባለሥልጣናት ዐውቀውት እና ፈቅደው ያደረጉት የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው፡፡”
በማይካድራ የተፈጸመው ግፍ ከጥቅምት 30 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት ይታሰባል፡፡ ይዘከራል፡፡ እነኾ ጊዜው ደርሶ ዘንድሮም ግፍ የተፈጸመባቸው ቀናት እየታሰቡ፣ እየተዘከሩ ነው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!