
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ሰላምን ከመፍጠርና ከመገንባት ጋር የተያያዙ አጀንዳዎች የጋራ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የሰላም ምሰሶ መሰረት የሚቀመጠውም ሆነ የሚፀናው በጋራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ይርጋ፤ የሰላም እሴቶች የሚገነቡት፣ የሚጠበቁትና ዘላቂነታቸውም የሚረጋገጠው በእያንዳንዳችን ጥረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ይርጋ ሰላም ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮቻችን ባሻገር የሆነ የሰብአዊነት ከፍተኛ እሴት እንደመሆኑ መጠን የሁሉንም እውነተኛ ፍላጎት ይጠይቃልም ብለዋል፡፡ ሰላም የሁሉንምና በምንም አግባብ የማይረታ ጥረትን እንደሚፈልግ የገለፁት የጽ/ቤቱ ኃላፊ ከልብ የሚመነጭና ቁርጠኝነትን የተላበሰ፣ ለሰላም መስፈን የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የሚቀመጥን የትኛውንም ተግባር ለመፈፀም መስዋዕትነትን ለመክፈል መነሳትን እንደሚሻ ገልፀዋል፡፡
የሀገርና የሰላም ጉዳይ የማይመለከተው ዜጋና የማይዳስሰው የማኅበረሰብ ክፍል የለም፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ፣ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ለሁሉም ፍጥረት ሰላም አስፈላጊና ወሳኙ ጉዳይ ነው፤ ስለሆነም ለሰላም መስፈን ሁሉም ባለድርሻ አካል ሊሠራ ይገባልም ብለዋል፡፡
መንግሥት ለሰላም መፈጠር፣ መገንባትና መፅናት የሚሠራውን ተግባር በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎች፣ በሴቶች፣ በወጣቶች፣ በምሁራን፣ በንግዱ ማኅበረሰብ እንዲሁም በልዩ ልዩ ተቋማት አማካኝነት እየተደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!