
ባሕር ዳር: ኅዳር 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ የማንዱራ ወረዳ በጫካ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጠቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላም ተመልሰዋል።
በማንዱራ ወረዳ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ሲገቡ የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በገነተ ማሪያም ከተማ በመገኝት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የመተከል ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ለሜሳ ዋውያ ታጣቂዎቹ የሰላም አማራጭን በመቀበል ወደ ኅብረተሰቡ መመለሳቸው የቀጣናውን ሰላም በዘላቂነት የተረጋጋ እንዲኾን ያደርገዋል ብለዋል።
ተመላሾችን በተማሩበትና ፍላጎታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ለማሰማራት መንግሥት ዝግጁ መኾኑን አቶ ለሜሳ ተናግረዋል።
በመኩሪያው ዚፋሃ እና በመኮነን ፋኖ በሚባሉ ግለሰቦች ሲመራ የነበረው የጉህዴን ታጣቂዎች ቡድን በተደረገው ከፍተኛ ጥረት ውይይት ተደረጎ የሰላም ስምምነት መደረጉ ተገልጿል።
ይህ ታጣቂ ኀይል በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ጫካ ውስጥ መቀመጫቸውን አድርገው በአዋሳኝ አካባቢዎች ስጋት ሲፈጥሩ ቆይተዋል። በውይይት መምጣቸው ለኅብረተሰቡ ሰላምና ልማት ለመግባት የሀገር ሽማግሌዎችና መሪዎች በተገኙበት ከሰላም ተመላሾች ጋር በጉሙዝ ብሔረሰብ ባሕላዊ የእርቅ ሥነ ሥርዓት ማካሄዳቸውን ከመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!