ቼልሲ እና ማንቸስተር ሲቲ በስታምፎርድ ብሪጅ ይጫወታሉ።

54

ባሕር ዳር: ኅዳር 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በ12ኛ ዙር ቼልሲ ከማንቸስተር ሲቲ በስታምፎርድ ብሪጅ ምሽት 1ሰዓት ከ30 ይጫወታሉ፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ከዛሬው ጨዋታ በፊት 43 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ቼልሲ 15 ጊዜ አሸንፏል፡፡ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ 25 ጊዜ ረትቷል፡፡ በሦስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ለአምስተኛ ጊዜ ዋንጫ ያነሱት ሲቲዎቹ በአጠቃላይ አምስት ተከታታይ ጨዋታዎችን አሸንፈዋል።

ቼልሲ በ2021 ከሜዳው ውጪ 2 ለ 1 ካሸነፈ በኋላ ከማን ሲቲ ጋር ባደረጋቸው የመጨረሻ አራት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ተሸንፏል።

ቼልሲ በ2023 በሜዳው ባደረጋቸው ስምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ተረትቷል።

ጋሪ ኔቪል ቼልሲ ማንቸስተር ሲቲን ሊያሸንፍ እንደሚችል በፉት ቦል ለንደን ድረ ገጽ ላይ ጽፏል፡፡ ታዋቂ የስፖርት ተንታኞች ከዚህ የሒሳብ ስሌት ተነስተውም ዛሬም በስታምፎርድ ብሪጅ የሚያደርገውን ጨዋታ ይሸንፋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሰማያዊዎቹ በሊጉ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በለንደን ደርቢ ቶተንሃምን 4 ለ 1 በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል በሁለተኛው አጋማሽ ኒኮላስ ጃክሰን የ22 ደቂቃ ሃትሪክ ሠርቷል።

የቸልሲው አሠልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቸቲኖ ስለተጋጣሚያቸው ክለብ ሲናገሩ “ማንቸስተር ሲቲን ‘የዓለማችን ምርጡ ቡድን ነው’ ሲል አሞካሽቷቸዋል፡፡ ምርጥ የአሠልጣኞች ስታፍም አለው፡፡ የምርጥ አሠልጣኝ ባለቤትም ነው፡፡ ምክንያቱም በውድድር ዓመቱ እያሳዩት ያለው ውጤት በደንብ እየሠሩ ስለመኾናቸው ይናገራልና ነው” ብለዋል፡፡

“ነገር ግን “አሉ ፖቸቲኖ “ክለቤ ከእነሱ ያነሰ አቋም አለው እያልኩ አይደለም፤ ተጫዋቾቼ ጥሩ ልምምድ ሠርተዋል፤ ጥሩ የማሸነፍ ሥነ ልቦና ሰንቀዋል፡፡ ጨዋታው ደግሞ በሜዳችን ነው፡፡ እናም ዛሬ የምንጫወተው በጥሩ ጨዋታ ለማሸነፍ ነው ፤ እመኑኝ እናሸንፋለን” ብለዋል፡፡

አሠልጣኙ የቸልሲን የመጀመሪያ አሰላለፍም ጠቁመዋል፡፡

ቼልሲ 11 ጨዋታዎች አድርጎ በአራቱ ሲያሸንፍ በአራቱ ደግሞ ተሸንፏል፡፡ በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል፡፡ በመኾኑም በአምስት ንጹህ ግብ እና በ15 ነጥብ በ10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ሲቲ በዚህ የውድድር ዓመት በተደጋጋሚ በርካታ ዋንጫዎችን በማንሳት ይታወቃል፡፡ የፕሪሚየር ሊግ፣ የኤፍኤ ካፕ እና የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን በማንሳት ታሪኩን በደማቅ ቀለም ያጻፈ ክለብ መኾኑን ልብ ይሏል፡፡

አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ለቸልሲ ከፍተኛ ግምት ሰጥተው እንደተዘጋጁ ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ በፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮን ለመኾን እየተጫወተ ያለ ነው፤ ፖቸቲኖ ደግሞ ጨዋታ በጣም ማንበብ እና መምራት የሚችል አሠልጣኝ ነው፤ የእኛን ክፍተትም ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ሊፈትነን እንደሚችል ዐውቀን ተዘጋጅተናል፤ ማሸነፍ እናሸንፋለን፤ ስናሸንፍ ግን ማራኪ ጨዋታ አሳይተን መኾን እንዳለበት ከልጆቼ ጋር ተነጋግረናል ብለዋል፡፡

በሌሎች የዛሬ መርሐ ግብሮች ቀን 11ሰዓት ላይ አስቶንቪላ ከፉልሀም፣ ብራይተን ከሼፊልድ ዩናይትድ፣ ሊቨርፑል ከ ብሬንትፎርድ፣ ዌስትሃም ከኖቲንግሃም ፎሬስት ይጫወታሉ፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጉራሽ ፈላጊ ጎሮሮዎች፣ እጅ ተመልካች ዓይኖች”
Next articleበመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የጉህዴን ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ተመለሱ።