
ባሕር ዳር: ኅዳር 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አርሰው የሚጎርሱት፣ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሚተርፉት፣ የተራበን የሚያበሉት፣ የተጠማን የሚያጠጡት፣ የታረዘን የሚያለብሱት፣ ከጎተራቸው የማያጡት፣ ከመሶባቸው የማያጎድሉት ዛሬ ላይ ሁሉን አጥተዋል፡፡ ወደ ጎተራቸው የሚወርድ እህል ተቸግረዋል፤ በሞሶባቸው የሚሞላ እንጀራ ናፍቀዋል፡፡
ለወትሮው በጥቅምት እሸት ይቀጥፋሉ፣ ለአላፊ አግዳሚው እሸት ቅመስ እያሉ ያቀብላሉ፣ መንገደኛውን ሁሉ እሸት እያስጨበጡ፣ ወተት እያስጎነጩ ይሸኛሉ፡፡ እኒያ አስቀድመው መሬታቸውን አለስልሰው፣ ጥቁርና ነጩን የሚዘሩት ታታሪዎች ጥቅምት ሲያብት ፍሬ የሚያዩበት፣ እሸት የሚቀምሱበት፣ ለመሰብሰብ የሚዘጋጁበት፣ ቀድመው የደረሱትንም የሚሰበስቡበት፣ ሕዳር ወር ብቅ ሲል ማጭድ እና እጃቸው የማይለያይበት፣ ጎህ ሳይቀድ ወጥተው በጨለማ የሚገቡበት ጊዜ ነበር፡፡
ከባዶ መሬት ላይ አብቅሎ፣ ቅጠሉን አሳብቦ፣ አበባውን ባርኮ ፍሬ የሚሰጣቸውን፣ አንዲት የስንዴ ፍሬ መሬት ላይ ጥለው ብዙ አድርጎ የሚያስነሳላቸውን አምላካቸውን እያመሠገኑ ሲያጭዱ ይውላሉ፡፡ በመሸም ጊዜ አምላካቸውን እያመሠገኑ ይመለሳሉ፡፡ገበሬ ተስፈኛ ነው አምላኩን ተስፋ አድርጎ በባዶ መሬት ላይ ዘር ይበትናል፡፡ ገበሬ አማኝ ነው ፈጣሪውን አምኖ “ሞት እና ክረምት አይነሳንም” እያለ ይዘራል፤ ቅጠል፣ አበባ እና ፍሬም ይጠብቃል፡፡
አስቀድሞ ገና ሰማዩ ደመና ሲያዝል፣ አምላክ የምህረት ዝናብ ሲያዘንብ አርሶ አደር ከደስታ ላይ ደስታ ይጨምራል፡፡ አምላኩን እየደጋገመ ያመሠግናል፡፡ የምሕረት ዝናብ ከተሰጠው ሌላ አይፈልግም አምላኩን እያመሠገነ ያርሳል፣ ያንደፋርሳል እንጂ፡፡ ደመና በሰማይ ካልታየ፣ ዝናብ ካልወረደ፣ ምድር በእርጥበት ካልረሰረሰች ያን ጊዜ ሰማይ ይደፋበታል፤ ጭንቅ እና ሀሳብ ይበረታበታል፡፡
እነኾ በዚህ ወቅት ጭንቅ የበረታባቸው፣ ሀሳብ የበዛባቸው አርሶ አደሮች በርክተዋል፡፡ እንደ ወትሮው ሁሉ በማሳቸው የሚታጨድ ሰብል አልበቀለም፡፡ እሸት አልቀጠፉም፣ ለአላፊ አግዳሚውም አላቀበሉም፡፡ ምድር በልምላሜ አልረሰረሰችም፡፡ ፍሬም አልሰጠችም፡፡ እንደ ደረቀች ከረመች፡፡ እንደ ደረቀች ወራቱን አሳለፈች እንጂ፡፡
እኒያ በሕዳር ከሰፊ አውድማ እያፈሱ ጭነት የሚያበዙት፤ ገበያውን የሚያጠግቡት፤ በሀሳብ የናወዘውን ሁሉ የሚያረጋጉት ታታሪዎች እንኳን ገበያውን የሚያጠግቡበት ተሰናድቶ ወደ ተቀመጠው ጎተራ የሚያስገቡት አጥተዋል፡፡
እኒያ በሀሳብ የሚናውዘውን፣ ሰብል ይጠፋ ይኾን እያለ የሚጨነቀውን በሰፊው አምርተው የሚያስደስቱት እና ጭንቀቱን የሚያርቁት ብርቱዎች ዘንድሮ ግን ራሳቸው ተጨንቀዋል፤ ከምርት ላይ በምርት በሚደራርቡበት፣ ጎተራውን በነጭና ጥቁር በሚያጨናንቁበት በዚህ ወቅት የዕለት ጉርስ ፈልገዋል፡፡ እንጀራ እያሉ የሚያለቅሱ ልጆቻቸውን ዝም የሚያስብሉበት እህል ናፍቀዋል፡፡
በአማራ ክልል በተፈጠረው የዝናብ እጥረት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡ የሰው እጅ ተመልካች ኾነዋል፡፡ በክልሉ በተከዜ እና በአዋሽ ተፋሰሶች በተፈጠረው የዝናብ እጥረት እንስሳት የሚቀምሱት ልምላሜ አጥተዋል፡፡ ሰዎችም የሚጎርሱት ምግብ ተቸግረዋል፡፡ ብዙዎች አካባቢዎች በተከታታይ ዓመታት የዝናብ እጥረት ገጥሟቸዋል፤ ከአንደኛው ችግር ሙሉ ለሙሉ ሳይወጡ ለሌላ ችግር ተዳርገዋል፡፡
አሁን ላይ ጉራሽ ፈላጊ ጉሮሮዎች፣ እጅ ተመልካች ዓይኖች በርክተዋል፡፡ “አንድ ሰኔ የነቀለውን ሰባት ሰኔ አይመልሰውም” እንዲሉ አበው በሰኔ ማሳቸው ዘርን አልያዘችም እና የምህረት ዝናብ ምድሯን አረስርሷት፣ አርሰው፣ አምርተው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ድጋፍ ይሻሉ፡፡ የሰው እጅ ለመመልከት ይገደዳሉ፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን እየረዳሁ ነው ብሏል፡፡ ነገር ግን ካለው ሰፊ ችግር እና ክልሉ ከቆዬበት ተደራራቢ ችግር እገዛ እንደሚፈልግም ገልጿል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በክልሉ በተፈጠረው የዝናብ እጥረት ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች ላይ ድርቅ ተከስቷል ነው ያሉት፡፡ በተለይም በተከዜ ተፋሰስ የተከሰተው ድርቅ ከፍ ያለ ነው፡፡ በክልሉ ሰሜን፣ ማዕከላዊ፣ ደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ዋግኸምብራ ብሔረሰብ አስሥተዳደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ድርቅ የተከሰተባቸው መኾናቸውን አንስተዋል፡፡ በክልሉ በአጠቃላይ በዘጠኝ ዞኖች እና 43 ወረዳዎች ላይ ድርቅ መከሰቱንም አመላክተዋል፡፡
በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወገኖች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋልም ተብሏል፡፡ በዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተው የድርቅ ሽፋን ከፍተኛ መኾኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ወገኖችን እየደገፉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የከፋ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ቅድሚያ ሰጥቶ መደገፍ እንደሚያሻም አመላክተዋል፡፡ ኮሚሽነሩ እንደገለጹት ማኅበረሰቡ ሰፊ ችግር ነው ያለበት፣ በአማራ ክልል ያለው ችግር በጣም ውስብስብ ነው፣ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ችግሮች አሉ፤ ሰፊ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ በሕወሓት ወረራ ጦርነት ክልሉ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፤ የተፈናቀሉ ወገኖች ሙሉ ለሙሉ ሳይቋቋሙ ድርቅ ተጨማሪ ችግር አምጥቷል ነው ያሉት፡፡
ተፈናቃይ አለ፤ በጦርነት የተጎዱትን መልሰን አላቋቋምንም፤ አሁን ደግሞ ድርቅ አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ ውስጥ የጸጥታ ችግር አለ፤ ይህ ሁሉ ተደራርቦ ማኅበረሰቡን ወደ ውስብስብ ችግር አስገብቶታልም ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ከፍተኛ የኾነ ድጋፍ እንደሚፈልግም ገልጸዋል፡፡ ችግር አለ፣ ችግሩን እያዩ ደግሞ ሁሉም ድጋፍ ያደርጋሉ ብለንም እንጠብቃለን ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፡፡ የተሻለ ምርት ካመረቱ አርሶ አደሮች፣ ከባለሀብቶች፣ ከነጋዴዎች፣ ከዲያስፖራዎች እና ከመንግሥት በጀት በማሰባሰብ ችግሩን ለመፍታት እንደ መፍትሔ የያዙት አማራጭ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በረጂ ድርጅቶች የሚሰጠው እርዳታ ከወረኃ ግንቦት/2015 ዓ.ም ጀምሮ ቆሟል፡፡ እርዳታ እየተሰጠ ያለው በመንግሥት ነው፣ መንግሥት ይሄን ሁሉ መሸፈን አይችልም፣ ሁሉም ድጋፍ ማድረግ አለበት፣ ለማንም የሚተው አይደለም፣ ይሄ የሰብዓዊነት ጉዳይ ነውም ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡
በክልሉ የሚቀርበው ድጋፍ በቂ ካለመኾኑም በላይ የተገኘችውን ለተጎጂዎች ለማቅረብ የጸጥታ ችግር ፈተና መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ እጥረቱ ላይ በታሰበው ጊዜ ለሕዝብ አለማድረስ ተጎጂዎችን የበለጠ እየጎዳቸው ነው፡፡ የእርዳታ እህል ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሾፌሮች እየታገቱ የጫኑት እየተዘረፈ እየተሸጠ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
ማንኛውም ለሕዝብ አስባለሁ የሚል ሁሉ የሰበዓዊ እርዳታዎችን መጠበቅ አለበት፤ ይህ አይነቱ አካሄድ ተገቢ አይደለም፤ ለሕዝብ አስባለሁ የሚል ሁሉ ለሕዝብ የሚቀርብን የሰበዓዊ ድጋፍ በየትኛውም ቦታ ማደናቀፍ የለበትም ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡ ሰብዓዊ ድጋፍ በየትኛውም ችግር ውስጥ ቢኾን ማለፍ አለበት፣ ሕዝቡም የሰብዓዊ ድጋፎች እንዳይደናቀፉ፣ ለተቸገሩ ወገኖች እንዲደርሱ መታገል ይገበዋል ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ ካላገዘ እና ካልተባበረ የሰበዓዊ ድጋፍ ማድረስ እንደማይችሉም ገልጸዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ የእንስሳት የመኖ እና የውኃ እጥረት አለ፤ የሕክምና እጥረትም አለ፤ ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ ለመስጠት ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሠራ መኾኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውንም ተናግረዋል፡፡ እንደ ክልል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት መኾኑን አንስተዋል፡፡ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሁሉንም ተሳትፎ የሚፈልግ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ሰብዓዊነት የሚሰማው፤ የሰዎች ረሃብ የሚርበው፣ የሰዎች መጠማት የሚጠማው፣ የሰዎች መቸገር የሚቸግረው ለተቸገሩት ያለውን ሁሉ ያድርግ። በድርቅ የተጎዱት እርዳታ እየጠበቁ ነውና፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!