
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክፍሎች የመጡ መሪዎች ሥልጠና በባሕር ዳር ተጀምሯል። በመሪዎች ሥልጠና የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መለስ ዓለም፣ የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አቶ ይርጋ ሲሳይ መንግሥት ጠንካራ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ሥልጠና እየሠጠ መሆኑን ተናግረዋል። “የምንወዳትን እና የምናከብራትን ሀገራችንን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ ኢትዮጵያዊ አብቶሮነትን ማስቀደም ይገባል” ብለዋል።
በዘመናት በነበረው ጉዞ የነበሩ ክፍተቶችን መሙላት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ የምትፈልገውን አንድነት፣ አብሮነት እና ወንድማማችነት ማጎልበት እንደሚገባም አመላክተዋል። ለዚህም ሥልጠናው መልካም አጋጣሚ መኾኑ ገልጸዋል። በሥልጠናው ራስን በማሳደግ ሀገርን ለመምራት የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
በስሜት ሳይኾን በዕውነት እና በአንድነት የምንደጋፍበት እንዲኾን በትኩረት መከታተል ይገባልም ብለዋል። ልዩነትን በማጥበብ አንድነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል። ችግሮችን በወንድማማችነት እና በጋራ የመፍታት ባሕልን ማሳደግ የአሁኑ ትወልድ ኃላፊነት መኾኑንም ገልጸዋል።
“የክልሉ ሕዝብ እንግዳ መቀበል ባሕሉ ነው ያሉት አቶ ይርጋ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ወደ አማራ ክልል ስትመጡ ቅር ተሰኝታችሁ ይኾናል፤ በቆይታችሁ ግን አንመለስም እንደምትሉ አምናለሁ” ሲሉ ለሠልጣኝ አመራሮች ገልጸዋል። ምክንያቱ ደግሞ ሕዝቡ እንግዳ መቀበል እና ማስተናገድ ያውቅበታልና ነው ያሉት።
ሠልጣኞች በሰላም ገብተው፣ በሰላም ሠልጥነው፣ ሃሳብ አንሸራሽረው በሰላም እንደሚመለሱም ገልጸዋል። በጸጥታ ጉዳይ ሥጋት እንዳይገባቸውም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያን ውድቀት የሚመኝን ሃሳብ በመንቀፍ፣ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያመጣውን ሃሳብ በመደገፍ ለኢትዮጵያ ልዕልና መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። የአመራር አንድነት በመፍጠር ለኢትዮጵያ አንድነት መሥራት ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!