በአማራ ክልል ከ376 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ይከናወናል።

59

ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ376 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለማሳተፍ መታቀዱን ጠቁመው ባለፈው ዓመት የተከናወነው ተመሳሳይ ተግባር ውጤታማ መሆኑም ተመልክቷል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አልማዝ ጊዜው (ዶ.ር) የዘንድሮውን የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ካለፉት ዓመታት ልምድ መወሰዱን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የአፈር ለምነትን በመጠበቅ የሰብል ምርታማነት በሄክታር እስከ 8 ኩንታል ማሳደግ እንደተቻለ በቢሮው በተካሄደ ጥናት መታወቁን ገልጸዋል።

እንዲሁም በ2012 ዓ.ም 14 ነጥብ 6 በመቶ የነበረው የክልሉ የደን ሽፋን ወደ 15 ነጥብ 7 በመቶ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማድረጉንም አመልክተዋል።

ተፋሰሶችን በማልማት እና በማስፋት ለወጣቶችም የሥራ እድል መፍጠሪያ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው ባለፈው ዓመት ብቻ ከ24 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች በተፋሰሶች የሥራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

የተገኙ ልምዶችን በመጠቀም ዘንድሮ በተመረጡ 9 ሺህ 60 ተፋሰሶች ላይ 376 ሺህ 561 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት መጀመሩን አስታውቀዋል።

ከ307 ሺህ በላይ ቀያሽ አርሶ አደሮች እና ከ3 ሚሊዮን በላይ የልማት መሳሪያ የልየታ ሥራ ለማከናወን በሂደት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር አልማዝ የልማት ሥራውም ጥር 2016 ዓ.ም አጋማሽ እንደሚጀመር አስረድተዋል።

በዚሁ የበጋ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራም ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በማሳተፍ በአማካይ ለ23 ቀናት ሥራውን ለማከናወን ታቅዷል፡፡

በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በ357 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ መከናወኑ ተወስቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመንግሥት አመራሮች ሥልጠና በባሕር ዳር የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።
Next articleኢትዮጵያ ከጂቡቲ እና ሶማሊያ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄደች።