
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮሌራ ወረርሽኝ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በአማራ ክልል ከሐምሌ 7/2015 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ወረዳዎችን አዳርሷል። በተለይም ደግሞ የምዕራብ አማራ አካባቢዎች ሥርጭቱ ከፍ ያለ እንደነበር የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ገልጸዋል።
በ11 ወረዳዎች የኮሌራ ወረርሽኝን መቆጣጠር ቢቻልም በ24 ወረዳዎች አሁንም የወረርሽኝ ሥርጭቱ መኖሩ ተገልጿል፡፡ ወረርሽኙ አሁን ላይ ከአቅም በላይ አለመኾኑን ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።
በክልሉ እስከ ጥቅምት 25/2016 ዓ.ም ድረስ ከ4 ሺ 6 መቶ የሚኾኑ ሰዎች በኮሌራ በሽታ ተይዘዋል፡፡ 86 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ሰዎች በወረርሽኙ የሞቱት በወቅት በክልሉ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት እንደልብ ተዘዋውሮ መርዳት ባለመቻሉ እንደኾነም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ወራት የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ የመቆጣጠር ሥራ ቢሠራም ከሰሞኑ በሰሜን ወሎ ዞን እና በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር 300 ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡
የበሽታው የመዛመት አቅም ከፍተኛ መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ ኢንስቲትዩቱ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ወረረሽኙ ጉዳት እንዳያደርስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ወረርሽኙ ወደ ሌሎች ወረዳዎች እንዳይስፋፋ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት እንዲሁም ክልሉ ወረርሽኙ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች የሕክም ግብዓት እየቀረበ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ክትባት ማግኘታቸውን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ አሁንም በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ክትባት መስጠት እንዲቻል ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ለበሽታው አጋላጭ የኾኑ ውኃ እና ምግቦችን በጥንቃቄ መጠቀም፣ የግል እና የአካባቢ ንጽሕናንም በአግባቡ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
የጤና ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ መኾኑን በመገንዘብ የሕክምና ግብዓቶች ወደ ማኅበረሰቡ በፍጥነት እንዲደርሱ ሁሉም ትብብር እንዲያደርግ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!