“የከተማችን ነዋሪዎች መሰረታዊ ችግሮችን በመፍታት በሙሉ አቅማቸው ማምረት የሚችሉበትን መንገድ ለመፍጠር እንሠራለን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

21

ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ከ14 ሺህ በላይ ሰዎች የከተማ ሴፍትኔት ሥራ ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡

ወይዘሮ ሰላም ግሩም በአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የማራኪ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ሰላም በሴፍትኔት ከመደራጀታቸው በፊት ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ የቤት ውስጥ ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡

በዚህም የሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን ለማሥተዳደር ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ወይዘሮ ሰላም በዚህ ሥራ በመሳተፋቸው “የሥራ እና የቁጠባ ባሕላችን ዳብሯል፤ እንዲሁም በከተማ ግብርና ሥራ በመሳተፍ ተጨማሪ ገቢ እያገኘን ነው”
ብለዋል፡፡ እስካሁንም 415 ሺህ ብር መቆጠብ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ የሱፍ ጥጋቡ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በጣና ክፍለ ከተማ ራሥ አገዝ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በሥራው እየተሳተፉ ነው፡፡

በዚህ በመሳተፋቸው የገጠማቸውን የኑሮ ውድነት በትንሹም ቢኾን መቋቋም ችለዋል፡፡ ወቅቱ ጥሩ ባለመኾኑ ሠርተው ቤተሰባቸውን ለማሥተዳደር ተቸግረው ነበር፡፡ አሁን በነፍስ ወከፍ ከሚያገኙት ገቢ በተጨማሪ በከተማ ግብርና እየተሳተፉ እና የተሻለ ገቢ እያገኙ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሥራው የአካባቢ ጽዳት፣ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ የከተማ ግብርና እንደሚያካትት አቶ የሱፍ ተናግረዋል፡፡

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማ ሴፍትኔት አስተባባሪ እመቤት መንግሥቱ ሥራው በ2014 ዓ.ም እንደተጀመረ ተናግረዋል፡፡

በከተማ ውስጥ የሚገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን በመመልመል በደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በከተማ ግብርና፣ በከተማ ጽዳት እና ውበት እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሳተፉ መደረጉን ወይዘሮ እመቤት አንስተዋል፡፡

ሥራው ከእለት ገቢ በተጨማሪ የሥራ ባሕልን በማዳበር እና ተጨማሪ ሥራ በመሥራት ገቢ የማግኘት ልምዳቸው እንዲዳብር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በስድስቱም ክፍለ ከተማ የተጀመረው የሴፍትኔት አተገባበር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለ ባካሄዱት ጉብኝት መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሰዎች የሥራ ባሕላቸውን እንዲያዳብሩ እና ቁጠባን ባሕል አድርገው የራሳቸውን ሕይዎት እንዲመሩ መደረጉ በጥሩ ጎን የሚታይ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ የከተማዋን ገጽታ ከመገንባት በተጨማሪ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው ርብርብ አንዱ አካል እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡

ከተማ አሥተዳደሩ የተጠናከረ ድጋፍ በማድረግ ሰዎች ኑሮአቸውን በተሻለ መንገድ የሚመሩበትን መንገድ እንደሚያመቻቹም ተናግረዋል፡፡

መሰረታዊ ችግሮችን በመፍታት ሰዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት የሚችሉበትን መንገድ ለመፍጠርም እንሠራለን ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፡፡

እግረ መንገዱንም በከተማዋ ምን ያክል የከተማ ግብርና አቅም እንዳለ ያየንበት እና ሥራ አጥ ወጣቶችን በዘርፉ ለማሰማራት በር የከፈተልን ነውም ብለዋል፡፡

ዘጋቢ ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo: Onkoloolessa 30/2016
Next articleየኮሌራ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡