በብሔረሰብ አስተዳደሩ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ከ75 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተባለ፡፡

20

ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አብርገሌ ወረዳ ባሉ ሦስት ቀበሌዎች ላይ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ5 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ።
ወይዘሮ መይቱ ተክለይ ሦስት ሕጻናትን ታቅፈው መጠለያ ጣቢያ ከተቀመጡ ሁለት ወራት አልፏቸዋል።

ወይዘሮ ወጋህታ ተገኝ ሕጻን ይዞ በመጠለያ ጣቢያ መቀመጥ ለእናቶች አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡ 10 ቤተሠባቸውን ይዘው ቤታቸውን ዘግተው እንደመጡ ገልጸዋል።

ወይዘሮ ወጋህታ መንግሥት ከሁለት ወር በፊት ከሰጣቸው 15 ኪሎ ሰንዴ ውጭ የተደረገላቸው ድጋፍ እንደሌለም ተናግረዋል።

በአብርገሌ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የምግብ ዋስትና እና የአደጋ መከላከል ቡድን መሪ አለነ ታደሰ በበኩላቸው በወረዳው በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ27 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡

በድርቁ ምክንት ቀያቸውን ለቀው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለተሰደዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች መጠለያ ከማዘጋጀት ውጭ ድጋፍ ማድረስ አልቻልንም ብለዋል።

አሁን ላይ በዞኑ ምግብ ዋስትና በኩል 200 ኩንታል ፊኖ እና ፋፋ እንደገባ ገልጸው በአፋጣኝ እንደሚያከፋፍሉም ተናግረዋል።

ለቀጣይም የችግሩን ግዝፈት በመረዳት መንግሥት አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሉ ሦስት ወረዳዎች ማለትም ስሃላ ሰየምት፣ አብርገሌ እና ዝቋላ ወረዳዎች ስር ባሉ 26 ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ75 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በክልሉ በተከሰተው የዝናብ እጥረት በርካታ አካባቢዎች ላይ ድርቅ መከሰቱን ገልጸዋል። በተከዜ ተፋሰስ እና አዋሽ ተፋሰሶች ደግሞ ድርቁ መጠነ ሰፊ መኾኑን ተናግረዋል።

1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም አብራርተዋል። ለ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ወገኖች መንግሥት ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም አስረድተዋል።

እየተደረገው ያለው ድጋፍ በቂ አለመኾኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አንፈልጋለንም ብለዋል። መላው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲየደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በልማት የሚያስተሳስር ግዙፍ ፕሮጀክት ነው” ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ
Next articleከሥልጠናው ባሻገር የጎንደርን የመስህብ ስፍራዎች የመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸው ሠልጣኞች ተናገሩ።