“የግፍ ደም የፈሰሰባት፣ የዘር ፍጅት የተፈጸመባት”

141

ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግፍ ደም የፈሰሰባት፣ የመከራ ድምጽ የተሰማባት፣ እናቶች አብዝተው ያለቀሱባት፣ ሕጻናት በዋይታ የተመሉባት፣ የጭካኔ ጥግ የታየባት፣ ያጎረሱ እጆች የተነከሱባት፣ ያለበሱ የተሰቃዩባት ምድር፡፡ ደጎቹ ያለ ሐጥያታቸው ተቀጡባት፣ እንግዳ ተቀባዮቹ ያለ በደላቸው የግፍ ጽዋ ተቀበሉባት፤ ተበዳይ ኾነው ሳለ እንደ በዳይ ተቆጠሩባት፣ ደግ አድራጊዎች ኾነው ሳለ እንደ ክፉ አድራጊ ታዩባት፡፡

እናት የአብራኳን ክፋዮች አጣች፤ ጧሪና ቀባሪዋን በግፍ ተነጠቀች፤ ልጆች ወላጆቻቸውን ተነጠቁ፤ በሞት ጥላ ሥር ተከበው ተጨነቁ፡፡ ምድሯ በደም ጎርፍ ተጥለቀለቀች፡፡ በጣረሞት ድምጽ ተመላች፡፡ በሬሳ ብዛት ተጨናነቀች፡፡ አዳኝ እና ከልካይ በሌላቸው ንጹሐን ዋይታ ተናወጸች፡፡ ጎዳናዎች በደም ታጠቡ፣ ለአስከሬን ማሳረፊያ ጠበቡ፡፡

ዘር ጠፋባት፤ ማንነት እየተጠየቀ የግፍ ግፍ ተፈጸመባት፤ የጭካኔ የመጨረሻው ጥግ ታየባት፡፡ ከሞታቸው አሟሟታቸው ያስጨንቃል፤ ከሞታቸው አገዳደላቸው ያሳቅቃል፡፡ ለምን ቢሊ አሰቃይተው ገድለዋቸዋል፤ ስቃያቸውን አብዝተው ነብሳቸውን ከስጋቸው ለይተዋልና፡፡

“አለኝ አለኝ እና በደረቁ ላጨኝ
መላጨቱ ሳይኾን አድራጎቱ ቆጨኝ” እንዳለ የሀገር ሰው ከሞቱ አሟሟቱ ያበሳጫል፤ አገዳደሉ ያስቆጫል፤ ከሞት የከፋ አማሟት፤ ከመግደል የከፋ አገዳደል ነበርና፡፡ ሰው በሰው ላይ እንደዛ ይጨክናል ተብሎ አይጠበቅም ነበር፡፡ እነርሱ ግን ከማሰብ እና ከማለም ሁሉ በላይ የኾውን አደረጉት፡፡

ሁልጊዜም ትታወሳለች፣ የመከራ ቀን ናትና ትታሰባለች፤ በደል የተፈጸመባት ናትና ትዘከራለች፡፡ ልጆች አይረሷትም፣ የልጅ ልጆችም አይዘነጓትም፡፡ ታሪክ በማይጠፋ ቀለም መዝግቧታል፣ ዘመናትን ተከትለው ለሚመጡ ትውልዶች ሁሉ ያቆያታል፤ እያነጠረ ያሳያታል ማይካድራ፡፡

ጥቅምት 30 በደረሰ ጊዜ የማይካድራ ጭፍጨፋ ይታወሳል፡፡ የአማራዎች ስቃይ ይዘከራል፡፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ክህደት ከተፈጸመበት በኋላ በአማራ ክልልም ጥቃት ተፈጽሞ ነበር፡፡ ነገር ግን የአማራ ክልል ጀግኖች ባደረጉት ራስን የመከላከል እና መልሶ የማጥቃት ጦርነት እቅዱን ፉርሽ አደረጉት፡፡

ጀግኖቹ የተቃጣውን ትንኮሳ ከማክሸፍ አልፈው ለተከዳው የሀገር ዘብ እና የሀገር ኩራትም ደረሱለት፡፡ ጋሻና መከታም ኾኑለት፡፡ በመልሶ ማጥቃት ምት በቆመበት መርጋት የተሳነው ቡድን በግፍ ያለ ማንነት ማንነት ሰጥቶ፣ ከእርስታቸው አፈናቅሎ መከራ ሲያደርስባቸው የነበሩ አማራዎችን ሌላ ጥፋት ደግሶላቸው ነበር፡፡ በመልሶ ማጥቃት እየገሰገሰ የነበረውን ጦር መቋቋም የተሳነው ቡድን አስቀድሞ በተዘጋጁ ገዳይ ቡድኖች አማካኝነት በንጹሐን ላይ ማንነት ተኮር ፍጅት አደረገ፡፡

በማይካድራ ከተማ የሚገኙ አማራዎችን ከቤታቸው እያደነ ጨፈጨፋቸው፤ የማይካድራ ጎዳናዎችን በደም መላቸው፤ በአስከሬን አጣበባቸው፡፡ “ወረራና መዋቅራዊ ዘር ማጥፋት በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት” በሚል ርእስ ለንባብ የበቃው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተጠናው የጥናት መጽሐፍ “የማይካድራ የዘር ጭፍጨፋ ሕወሓት በአደባባይ እና በግልጽ ከፈጸማቸው የዘር ጭፍጨፋዎች አንዱ ነው፡፡

ማይካድራ ላይ አማራዎች በአብዛኛው ድምጽ አልባ በኾነ መሳሪያ በዘራቸው ብቻ ተመርጠው ተጨፍጭፈዋል፡፡ በማይካድራ ጸረ አማራ ዘመቻው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በግልጽ እየተተገበረ የመጣ አደረጃጀቱም ከሕወሓት የጸጥታ ተቋም እንደ አንድ ትልቅ ዕቅድ ተይዞ በነጋዴዎች፣ በኢንቨስተሮች እና በፖሊስ ተቋም የተቀናጀ ሥራ የተፈጸመ ወንጀል ነው” ይላል፡፡

በማይካድራ በጠቅላላው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ እና ጠለምት አማራዎች ዘራቸው እየተመረጠ፣ ማንነታቸው እየተለየ ለዓመታት የግፍ በትር አርፎባቸዋል፤ የመከራ ዶፍ ወርዶባቸዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን፣ ልጆች ወላጆቻቸውን አጥተዋል፡፡

ለዓመታት በዘለቀው የግፍ አገዛዝ ብዙዎች መድረሻቸው ሳይታወቅ የአራዊት ሲሳይ ኾነው ቀርተዋል፡፡ በመከራ ብዛት ሀገራቸውን ጥለው ብን ብለው ተሰደዋል፡፡ የጥናቱ መጽሐፍ እንደሚያመላክተው ከማይካድራ ግልጽ እና የታቀደ ጭፍጨፋ አስቀድሞ ለጭፍጨፋው ስኬታማነት የሚረዳ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ከጥፋት የተረፉትን ዋቢ አድርጎ ሲገልጽ “ጥላቻና ዝግጅቱ ቀድሞ ነው የተጀመረው፡፡ አማራ የሚባልን ሕዝብ ለማጥፋት ቀደም ብለው ነው የጀመሩት” ይላል፡፡

በማይካድራ አማራዎች ላይ ከግድያዎች ሁሉ የከፋው ግድያ ከመፈጸሙ አስቀድሞ ለሞት የታጩት ሲመረጡ ሰንብተዋል፡፡ እንዴት እና መቼ እንደሚገደሉም ተለይተዋል፡፡ ለዚያም ይኾን ዘንድ የንጹሐንን ነብስ የተጠሙ ቡድኖችን አሰልጥነው አስገብተው ነበር፡፡

“ ዛሬ እሞት ነገ እሞት አላውቀውም እኔ …..” እንዲል የሀገር ሰው ሠርተው የሚበሉ፣ ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚሳሱ፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚታትሩ ደጋጎች የመታረጃቸው ገጀራ እየተሳለ እነርሱ ዛሬን እየሠሩ ነገን በተስፋ ይጠብቁ ነበር፡፡ ሞት እና ገዳይ በዙሪያቸው እያንዣበቡ ለግድያ እያመቻቿቸው እነዚያ ደጎች ሥራ ላይ ነበሩ፡፡

ገዳዮች መቼ እና እንዴት እንደሚገድሏቸው ሲያመቻቿቸው ሟቾች በዕለት ተግባራቸው ነበሩ፡፡ ጠዋት ታይተው ማታ እንደጤዛ ሊያረግፏቸው፤ ጠዋት ፈክተው ማታ እንደ ተልባ አበባ ሊያጠፏቸው፤ ወላጆችን ከሚወዷቸው ልጆቻቸው ጋር ሊለያዩዋቸው፣ ልጆችን ከሚሳሱላቸው ወላጆቻቸው ጋር ሊነጥሏቸው፣ በግፍ እያሳዩ ሊገድሉባቸው ሽርጉድ ላይ ነበሩ፡፡ አብረው በኖሩት መገደል እንደ ምን ያለ ግድያ ነው? ባጎረሱት እጅ ነብስን መነጠቅ እንደ ምን ያለ ግፍ ነው? አምነው በተጎራበቱት መከዳት እና በግፍ መወጋት እንደ ምን ያለ ክህደት ነው?

ማይካድራ ላይ የኾነውን ማሰብ እንጂ መንገር ያስቸግራል ይላሉ ያቺን መከረኛ ቀን በሰቆቃ ውስጥ አሳልፈው ከሞት የተረፉ ነፍሶች፡፡ “ይህን ያክል ግፍ ይፈጽማሉ አላልንም እንጂ በ2008 ዓ.ም ጀምሮ አንዳንድ ዝግጅቶች ነበሩ፡፡ የጥቅምት 30/2013 ዓ.ም እንኳን ፍጡር በኾነ አስተሳሰብ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ፈርኦን ያደረገውን አይነት ነው ያደረጉት፡፡ እኔ ምንም ያላደረገኝን ሰው ማረድ ይከብደኛል፡፡ እነዚህ ግን ሳጥናኤል ናቸው” ይሏቸዋል፡፡

የጥናት ውጤቱ እንደሚያስረዳው አስቀድሞ ነገር ያለ ማንነት ማንነት የተሰጣቸው፣ በተወለዱበት ምድር እንደ ባዕድ እና እንደ ባይተዋር የተቆጠሩ አማራዎች የሀገሬው እና የዓለም ሕዝብ ሁሉ ሳያውቅላቸው በግፍ ሲገደሉ ሲሰቃዩ ኖረዋል፡፡

ማይካድራ ላይ የደረሰባቸው የጭካኔ ጥግ ለዓመታት ያሳለፉትን ማሳያ መስታውት ነው፡፡ ከወልቃይት እስከ ጠለምት ድረስ በተዘረጋው ምድር ቁጣራቸው የማይታወቅ አማራዎች በግፍ ተግድለው በጀምላ የተቀበሩበት ብዙ ነው፡፡

ማይካድራ ላይ በግልጽ በአደባባይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ እና ጠለምት አማራዎች በድብቅ ሲጨፈጨፉ እንደኖሩ የሚያሳይ እና የሚያስረዳ ነው፡፡ “ ያለምንም ሕጋዊ መሠረት እና የሕዝብ ፍላጎት ወደ ትግራይ ክልል እንዲተዳደሩ በግድ የተካለሉት ወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት አካባቢዎች የሕወሓት ጭቆና ገፈት ቀማሾች ናቸው” ይላል ጥናቱ፡፡

የማይካድራን ጭፍጨፋ ለማከናወን ወጣቶች ተመርጠው የውሎ አበል እየተከፈላቸው ሰውን በገጀራ፣ በካራ፣ በፋስ እና በሌሎች ስለታማ መሳሪያዎች እንዴት መግደል እንዳለባቸው ሰልጥነዋል፡፡ ያጎረሷቸውን ለመግደል ሰለጠኑ፡፡ ያመኗቸውን ለመካድ ሰለጠኑ፡፡ የንጹሐንን ደም በግፍ ለማፍሰስ ሰለጠኑ፡፡

ከሞት የተረፉት ያን ጊዜ ሲያስታውሱ “ ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ከቀኑ ስምንት ሰዓት ነው የጀመሩት፡፡ እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጭፍጨፋ ላይ ነበሩ፡፡ ሀውዜን እና ሳምሪ የሚባሉ አበል እየተከፈላቸው በደንብ የሰለጠኑ ገዳይ ቡድኖች ተዘጋጅተዋል፡፡ ሲገድሉህም አማራ መኾንህን በመታወቂያ እያረጋገጡ ነው” ይላሉ፡፡ ቀን ጨለመባቸው፤ ሰማይ ተደፋባቸው፤ በረዶ ወረደባቸው፡፡ አንገታቸውን ለገጀራ ሰጡ፡፡ ነብሳቸው በገፍ አለፈች፡፡

በጎንደር ዪኒቨርሲቲ የተጠናው ጥናት እንደሚገልጸው ጭፍጨፋው ታቅዶበት የተደረገ ነው፡፡ “ የማይካድራ ጭፍጨፋ ፖለቲከኞች፣ የጸጥታ ኀላፊዎች እና የደኅንነት ሰዎች አቅደው፣ በጀት አዘጋጅተው፣ አሰልጥነው፣ ስምሪት ሰጥተው፣ መኪና አዘጋጅተው እና ዝርዝር መረጃ ይዘው በተጠና መንገድ የፈፀሙት ሲኾን የሕወሓት ባለ ሥልጣናት አውቀውት እና ፈቅደው ያደረጉት የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው” ይላል፡፡

በማይካድራ የተካሄደው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በአይሁዶች ላይ እንደተካሄደው አይነት መኾኑንም ታሪክ አጣቅሰው ይገልጹታል፡፡ በማይካድራ ከልጇ እና ከእርሷ ፊት ባሏ በግፍ የተገደለባት እናት ያን ጊዜ ስታስታውስ “የምትሳሳለትን ባሌን ፊቴ ላይ ጨፍጭፈው ገደሉት፡፡ በመጨረሻም ጋዝ አምጥተው አጥንቱ እስኪቀር አቃጠሉት፡፡ ይህ ሁሉ ሲኾን እኔ እና ልጄ ለማልቀስ እንኳ የሚኾን አቅም ጨርሰን መሬት ላይ እየተንከባለልን ነበር” ብላለች፡፡

በማይካድራ ግድያ ብቻ አይደለም የተፈጸመው፡፡ ብዙዎች አካላቸው ጎድሏል፡፡ እግራቸውን ቆርጠዋቸዋል፣ እጃቸውን አሳጥተዋቸዋል፡፡

በግፍ የገደሏቸውን በግፍ በአንድ ጉድጓድ ቀበሯቸው፡፡ በጀምላ ገድለው በጅምላ አፈር መለሱባቸው፡፡ አፈር ያልመለሱባቸውን ለአራዊት ሰጧቸው፡፡ ጥቅምት 30 ለማይካድራ ጥቁር ቀን ናት፡፡ በዚህች ቀን ብዙዎች ከወደ ማይካድራ የጅምላ ጭፍጨፋ ተመልክተዋል፡፡ የጅምላ መቃብር አይተዋል፡፡ ወገኖቻቸውን በግፍ አጥተው ብቻቸውን የቀሩም በዚያች ቀን ታይተዋል፡፡

ያ ሁሉ መከራ አልፎ ማይካድራ ነጻነቷን ካገኘች ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ የግፍ ቀንበሯን አሽቀንጥራ ከጣለች ውላ አድራለች፡፡ አሁን በሚመስላት እየተዳደረች፤ በሚመስላት እየኖረች፤ በማንነቷ እየተከበረች ነው፡፡

ከዚያች የከፋች ቀን ተርፈው ታሪክ ለመንገር፣ የደረሰውን ግፍ ለመመስከር የበቁ ሁሉ በግፍ የተገደሉት፣ በጅምላ የተቀበሩትን እያስታወሱ ያስቧታል፡፡ ዳግም እንዳትደገም፣ ገዳዮች እና ከሃዲዎች ምድሯን እንዳይረግጧት ቃል ኪዳን በመግባት ያከብሯታል፡፡ ለማንነት የተከፈለውን ዋጋ እያሰቡ፤ ሲያምኑ የተካዱበትን ጊዜ እያንሰላሰሉ ይዘክሯታል፡፡ ገዳዮችን የቀጡላቸውን፣ ከሞት መንጋጋ ያወጧቸውን ጀግኖች እያስታወሱ ያከብሯታል፡፡ ማይካድራ የግፍ ደም የፈሰሰባት፤ የዘር ማጥፋት የተፈጸመባት፤ ዋይታና መከራ ያየለባት፣ አሁን ግን በእፎይታ ያለች ምድር፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከመላ ኢትዮጵያ የመጣችሁ የኢትዮጵያ ልጆች ናችሁና ቤታችን ቤታችሁ ነው” ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)
Next article“የሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በልማት የሚያስተሳስር ግዙፍ ፕሮጀክት ነው” ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ