
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ3ኛው ዙር የአመራሮች ስልጠና ለመሳተፍ ወደ ባሕር ዳር ከተማ ለገቡ እንግዶች ከደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ነዋሪዎች እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ናቸው በአየር ማረፊያው ተገኝተው አቀባበል ያደረጉላቸው።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች እንግዶች ወደ ከተማቸው ስለመጡ አመሥግነዋል፤ መልካም ቆይታ እንዲኖራቸውም መርቀው ተቀብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ እንግዶችን “እንኳን ደህና መጣችሁ” በማለት ተቀብለዋል። እንግዶች በባሕር ዳር ከተማ በሚኖራቸው የቆይታ ጊዜ ሁሉ ለሥልጠናቸው መሳካት የሚያስፈልገው ድጋፍ ሁሉ ይደረጋል ብለዋል።
“እንግዶቻችን በአንድ አዳራሽ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያን የምናይባቸው መልኮቻችን ናቸው” ሲሉም ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል። ባሕር ዳር ሰላማዊ ከተማ ናት፤ ከሁሉም ክልሎች ተውጣጥተው ወደ ከተማዋ የመጡ የመንግሥት አመራሮችን በሰላም ተቀብለናል፤ በሌላ ጊዜም ለመመለስ በሚያስችላቸው ፍቅር እንሸኛቸዋለን ብለዋል።
ከሥልጠናቸው ጎን ለጎን የባሕር ዳር ከተማን ልዩ ውበት፣ የማኅበረሰቡንም የካበቱ የሰው አክባሪነት እሴቶች በነጻነት እየተዘዋወሩ እንዲመለከቱ ከንቲባው ጋብዘዋል።
በእንግዶች አቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ሠልጣኝ አመራሮች ለሀገር እና ሕዝብ የሚጠቅም ዕውቀትና ልምድ ይዘው እንዲወጡ የሚያስችል ሥልጠና ይሰጣል ብለዋል።
በአማራ ክልል ውስጥ በባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻ ከተሞች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የመንግሥት አመራሮችን ተቀብለን በማስተናገድ ሥልጠናቸው የሰመረ እንዲኾን ቀድመን ተዘጋጅተናል ሲሉም ተናግረዋል።
“ከመላ ኢትዮጵያ የመጣችሁ የኢትዮጵያ ልጆች ናችሁና ቤታችን ቤታችሁ ነው፤ የአማራ ክልል ቆይታችሁ ያማረ እንዲኾን ከሕዝባችን ጋር ኾነን በፍቅር እናስተናግዳችኃለን” ሲሉም ሰልጣኝ የመንግሥት አመራሮችን ተቀብለዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!