“በድርቅና በሕገ ወጥ የኬሚካል ርጭት የንብ መንጋ ቁጥርና የማር ምርት እንዳይቀንስ ለአርሶአደሮች ድጋፎችን እያደረግን ነው” የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር

36

ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአማራ ክልል በንብ እርባታ ከሚታወቁ አካባቢዎች አንዱ ነው። በዘንድሮ ዓመት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ በኾኑ ምክንያቶች በስፋት ይመረት የነበረው የማር ምርት መቀነሱ ተገልጿል።

በዝቋላ ወረዳ 02 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወለላ ወልደሥላሴ 200 የንብ ቀፎ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ በዘንድሮው ዓመት አካባቢያቸው ላይ ከተከሰተው ድርቅ በተጨማሪ አካባቢው ፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካል በመረጨቱ ምክንያት የማር ምርት አለመገኘቱን ተናግረዋል።

አርሶአደሩ ባለፉት ዓመታት ከ300 ኪሎ ግራም በላይ ነጭ ማር እና ከ500 ኪሎ ግራም በላይ ቀይ ማር ይገኝ እንደነበር ገልጸዋል። ዘንድሮ ግን 10 ኪሎ ግራም ማር ብቻ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ይህም እንደ ገበያው ኹኔታ ከ200 ሺህ ብር በላይ ገቢ ያገኙ የነበረውን ዘንድሮ ማጣታቸውን ገልጸዋል።

የዝቋላ ወረዳ እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መስፍን በላይ በዘንድሮ ዓመት ከ144 ቶን በላይ የማር ምርት ለማግኘት አቅደው እስከ ጥቅምት 2016 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ 65 ቶን ብቻ መመረቱን ተናግረዋል፡፡ የባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ከተመረተው የማር ምርት ጋር ሲነፃፀር በ114 ቶን መቀነሱን አስረድተዋል።

ኀላፊው ለማር ምርት መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶቹ በወረዳው የተከሰተው ድርቅ እና ሰው ሠራሽ የኾነ የፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካል ሕገ ወጥ በኾነ መንገድ ንቦች ከሚገኙበት አካባቢ መረጨት ነው ብለዋል። ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ተቋማቸው እየሠራ ቢኾንም የባለድርሻ አካላት እገዛ አናሳ መኾኑ ችግሩ እንዲስፋፋ አድርጓል ብለዋል።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንስሳትና ዓሣ ሃብት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የእንስሳት እርባታና የመኖ ልማት ቡድን መሪ ወይዘሮ ለምለም ማሞ በብሔረሰብ አሥተዳደር ደረጃ 1ሺህ 350 ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ እስከአሁን ድረስ 158 ቶን ብቻ ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።

ቡድን መሪዋ የማር ምርቱ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት መቀነሱን ገልጸዋል፡፡ የፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካሉ መረጨት ከጀመረ ወዲህ የንብ መንጋው ቁጥርም እየቀነሰ መጥቷል ነው ያሉት። ችግሩን ለመቅረፍም ከአሥተዳደር ምክርቤቱ ጋር እየተሠራ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ በድርቁ ምክንያት የንብ መንጋው ቁጥር እንዳይቀንስ ንብ ለሚያንቡ አርሶአደሮች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- ሰሎሞን ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ወጣቶች የሰላምን አማራጭ በመከተል ለአካባቢያቸው መረጋጋት እየሠሩ ነው” የጎንደር ዙሪያ ወረዳ አሥተዳደር
Next article“ከመላ ኢትዮጵያ የመጣችሁ የኢትዮጵያ ልጆች ናችሁና ቤታችን ቤታችሁ ነው” ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)