
ባሕር ዳር: ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ንጋት ኮርፖሬት በአማራ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የ20 ሚሊዮን ብር የምግብ ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉ በሰሜን ጎንደር ዞን እና በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ነው ተብሏል። በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በየዳ፣ ጃናሞራ፣ ጠለምት፤ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰሃላ ሰየምት እና አበርገሌ ወረዳዎች ላይ በተደጋጋሚ ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ወገኖች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል ነው የተባለው።
ድጋፉን ያስረከቡት የንጋት ኮርፖሬት የብራንዲግ፣ ማርኬቲንግ እና ኮምዩኒኬሽን ችፍ ኢፊሰር አሰግደው ሽመልስ ንጋት ኮርፖሬት ኢንቨሰትመንትን በማስፋፋት የምጣኔ ሀብት ለማምጣት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የምጣኔ ሃብት ለውጥ ለማምጣት ከሚያደርገው አስተዋጽኦ ባሻገር ለማኅበራዊ ልማት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ የሕዝብ ተቋም መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘለቄታዊ የምጣኔ ሃብት ለውጥን ለማምጣት ዓላማ ይዞ እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። ኮርፖሬቱ ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ማካበት መቻሉንም አመላክተዋል።
ንጋት ኮርፖሬት በተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እየተፈጠረ መኾኑን በመገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አመላክቷል። ንጋት የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት ነው ያሉት ችፍ ኦፊሳሩ ለሁሉም ዜጎች ማኅበራዊ ዋስትና መረጋገጥ ይሠራል ብለዋል። በክልሉ የተከሰተውን የድርቅ አሳሳቢነትን በመረዳት በ20 ሚሊዮን ብር 4 ሺህ 470 ኩንታል የምግብ ዱቄት ገዝቶ ለክልሉ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ማስረከቡም ተመላክቷል። ኮርፖሬቱ መሰል ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮች ለዕለት ምግብ መቸገራቸውንም ገልጸዋል። ከዚህ በላይ የከፋ ችግር የለምም ነው ያሉት፡፡ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ድጋፍ መደረጉንም አስገንዝበዋል።
ድጋፉ ለተጎዱ ወገኖች በፍጥነት እንዲደርስ በኮርፖሬቱ የትራንስፖርት ድርጅት አማካኝነት ይደርሳል ነው የተባለው። ንጋት ኮርፖሬት ከ2018 እስከ 2023 (እ.አ.አ) ባሉት ዓመታት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ለቁልፍ ማኅበራዊ ልማቶች አስተዋጽኦ ማድረጉም ተገልጿል።
በዓመት 133 ሚሊዮን ብር ለማኅበራዊ ልማት እያዋለ መኾኑንም አመላክተዋል። የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ኀላፊው የተደረገው ድጋፍ ከጉዳቱ አንጻር በቂ አለመኾኑንም ገልጸዋል።
ንጋት የተቋቋመበትን ሁለንተናዊ ተልዕኮ በብቃት እንደሚወጣ የገለጹት ችፍ ኢፊሰሩ የሚዲያ ተቋማት፣ የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች፣ የበጎ አድራጎት ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት እና መላው ኢትዮጵያዊያን በድርቅ ከተጎዱት ወገኖች ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በክልሉ በተከሰተው የዝናብ እጥረት በርካታ አካባቢዎች ላይ ድርቅ መከሰቱን ገልጸዋል። በተከዜ ተፋሰስ እና አዋሽ ተፋሰሶች ደግሞ ድርቁ ሰፊ መኾኑን ገልጸዋል።
1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል። ለ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ወገኖች መንግሥት ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም አስረድተዋል። ለተደረገው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል። እየተደረገው ያለው ድጋፍ በቂ አለመኾኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ ተደጋጋሚ እና ከፍተኛ ድጋፍ አንፈልጋለንም ብለዋል። መላው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲየደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!