“ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ ዳግም እንዳይከሰት ሁሉም ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል” የማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች

97

ሁመራ: ጥቅምት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በ2013 ዓ.ም ጥቅምት 30 በማይካድራ ከተማ በማንነታቸው አማራ በመኾናቸው ብቻ በርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙ የሚታወስ ነው።

በጥቅምት 30/2013 ዓ.ም የተሰዉ ንጹሐን ዜጎች 3ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ በማይካድራ ከተማ ዛሬ ታስቧል።

በመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መሪዎች፤ የዞን የሥራ ኀላፊዎች፤ የሃይማኖት አባቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በመታሰቢያ መርሐ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማይካድራ ከተማ ከንቲባ ሙሉጌታ መብራቱ “ለነጻነታችን መሥዋዕትነት የከፈሉ ንጹሐን ዜጎችንና ለሀገር ክብር በመቆማቸው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የተሰዉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን ሁሌም ስንዘክራቸው እንኖራለን ብለዋል።

ጥቅምት 30 የጨለማው ዘመን የተገፈፈበት የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ነጻ የወጣበት በመኾኑ ሰማዕታትን በማሰብ ይታወሳል ነው ያሉት።

አማራነት እንደ ጥፋት ተቆጥሮ ለበርካታ ዓመታት በስውር ሲጨፈጨፍ የቆየው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በአደባባይ በማንነቱ ብቻ ጭፍጨፋ እንደተፈጸመበት ያነሱት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊና የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ናቸው።

ጥቅምት 30ን ስንዘክር ለወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ነጻነት መሥዋዕትነት የከፈሉ ንጹሐን ሰማዕታትን እና ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ለሀገር ደጀን ሲኾኑ በክህደት በናወዙ የተሰዉ ጀግኖች የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን በማሰብ መኾኑን ተናግረዋል።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ዛሬም ነጻነቱንና የአካባቢውን ሰላም አስጠብቆ ይገኛል ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የማይካድራ ዓይነት ጭፍጨፋ ዳግም እንዲከሰት አንፈቅድም ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ለሦስት አስርት ዓመታት መዋቅራዊ ግፍና በደል ሲደርስበት እንደነበር አስታውሰዋል።

ጦርነት የሰውን ሕይወት የሚቀጥፍ ፣ አካል የሚያጎድል ፣ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያደቅ በመኾኑ እንደ ማይካድራ ያሉ የጅምላ መቃብሮችና ጭፍጨፋዋች ዳግም እንዳይከሰቱ ለሰላም ዘብ ልንቆም ይገባል ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ሰላም ወዳድና በአብሮነት የሚያምን ነው ብለዋል አቶ አሸተ።

ሰላም የሀገር አንድነት የሚጸናበት በመኾኑ ከጦርነትና ከግጭት ይልቅ ለሰላም ዘብ መቆም ይገባል ያሉት ደግሞ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ503ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ወርቅነህ ጉዴታ ናቸው።

ጥቅምት 24 እና ጥቅምት 30 በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ጉዳት ያደረሰ ነው ያሉት ብርጋዴር ጀኔራል ወርቅነህ ጉዴታ እንደዚህ ዓይነት ታሪኮች እንዳይደገሙ ሰላምን አበክረን ልናስቀጥል ይገባል ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎችም ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መኾኑን አንስተው እንደ ማይካድራና ጭና ያሉ ኢ-ሰብአዊ ተግባራት እንዳይደገሙ ለሰላም ልንቆም ይገባልም ብለዋል።

ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ከ1 ሺህ 600 በላይ ንጹሐን የአማራ ተወላጆች መጨፍጨፋቸው የሚታወስ ነው።

ዘጋቢ ፡- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“60 ሚሊዮን ብር መድበን የምግብ ሸቀጥና እህል ለማቅረብ እየሠራን ነው” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር
Next articleበዩሮፓ ሊግ ዌስትሃም ከኦሎምፒያኮስ ዛሬ ይጫዎታል።