“60 ሚሊዮን ብር መድበን የምግብ ሸቀጥና እህል ለማቅረብ እየሠራን ነው” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር

39

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ የሰላም ችግር ላይ ከባለሀብቶችና ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት አድርጓል።

በከተማ አሥተዳደሩ ባለፉት ወራት ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ክልል የጸጥታ ኀይል እና በሕዝቡ ጥረት መሻሻል ቢታይበትም ለዘላቂ ሰላም ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይቱ ማስፈለጉ ተነስቷል።

በሰላም እጦቱ የዜጎች ሞት፣ የንብረት ውድመት፣ የማኅበራዊ ግንኙነት መቋረጥ፣ የሥራ አጥነት መስፋፋት እና የኑሮ ውድነት መባባስን ማስከተሉ ተገልጿል።

ኢንዱስትሪዎች ለማምረት ጥሬ ዕቃ ማስገባት ያልቻሉበት፤ ያመረቱትን ለመሸጥ የተቸገሩበት ሁኔታ ስላለ ይህ ችግር መልሶ እንዳይባባስ የንግዱ ማኅበረሰብ ሚና ከፍተኛ ስለመኾኑ ተጠቁሟል።

ተወያዮች በበኩላቸው ውይይት መደረጉ ጠቃሚ መኾኑን ገልጸዋል። አንድ እንድንኾን እና ችግሮቻችንን በሰላም ተመካክረን እንድንፈታ አድርጉን ሲሉም አሳስበዋል።

በጊዜ ቤታችን ካልገባን በስተቀር ሰላም አለ ማለት አይቻልም፤ የዜጎች ከቦታ ቦታ እንደልብ መንቀሳቀስ አለመቻል ችግር መፈታት አለበት ሲሉም ያለውን ችግር አብራርተዋል።

ተወያዮች ከግጭቱ በፊትም ኾነ ከተከሰተ በኋላ እየተስፋፉ ያሉ ችግሮችን ሲገልጹ እንዳሉት፦

👉 የአገልግሎት አሰጣጡ ድክመት ኢንቨስትመንትን ስላዳከመው የሥራ ዕድል ፈጠራው ተዳክሟል

👉 የመሬት ወረራው ተባብሶ ቀጥሏል

👉 የኑሮ ውድነትና የቤት ኪራይ ዋጋ ማሻቀብ ነዋሪውን እያማረረው ነው ብለዋል።

ስለኾነም ችግሮችን ከግጭት ይልቅ በውይይት መፍታት ይገባል ነው ያሉት።

ሚዲያዎች እውነተኛና ሚዛናዊ መረጃ እንዲያስተላልፉ ያሳሰቡት የውይይቱ ተሳታፊዎች ስለ ሰላም በማውራት ብቻ ሰላም ሊመጣ አይችልምና መሪዎች ሰላም እንዲሰፍን የሕዝቡን ስሜትና ፍላጎት ተረድቶ እንዲሠራ አሳስበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከሕዝብ ጋር እየተወያየን ያለነው ሰላሙ የሁላችን እንዲኾን ነው ብለዋል። የአማራ ክልል መንግሥት የሕዝቡን ችግሮች ለመፍታትና ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።

የከተማው ጸጥታ በዘላቂነት እንዲጸና ማኅበረሰቡ ኀላፊነት ወስዶ መተባበር ይጠበቅበታል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ብልሹ አሠራር እንደሚስተካከል ተናግረዋል።

መብትን በግዢ እና በዘመድ አዝማድ ለማስፈጸም መሞከርንም ማኅበረሰቡ እንዲያስወግድ አሳስበዋል።

የአልሚዎችን ሃሳብ ሰምተን በኢንቨስትመንቱ ላይ ያለውን ማነቆ እናስተካክላለን፤ ወጣቶች ወደ ባለሃብትነት እንዲያድጉ አልመን እንሠራለንም ብለዋል።

በኑሮ ውድነቱ እና በቤት ኪራይ ዋጋ ማሻቀብ ሕዝብ መቸገሩን እንገነዘባለን ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ፤ ለቤት ኪራይ ጭማሪው ጥናት ተሠርቶ በቅርቡ መፍትሄው ይተገበራል ብለዋል። የመኖሪያ ቤት ማኅበራትም በቅርብ ጊዜ የግንባታ ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።

”የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል 60 ሚሊዮን ብር መድበን የምግብ እህልና ሸቀጥ ለማቅረብ እየሠራን ነው” ብለዋል

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጦርነትና ግጭት የሚሰብክና የፖለቲካ ሙቀት ቀስቃሽ ሚዲያን ከማምለክ ይልቅ ችግሮቻቸውን እየሞላን ለሰላም የሚሠሩትን ማጠናከር አለብን ነው ያሉት።

ኅብረተሰቡ ከአዋጊ ሚዲያ በስተጀርባ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው አካላት መኖራቸውን ተረድቶ ከሰላም ሰባኪ ሚዲያዎች ጎን እንዲቆምም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ወደ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ገብተው መማር እንደሚፈልጉ ተማሪዎች ገለጹ፡፡
Next article“ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ ዳግም እንዳይከሰት ሁሉም ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል” የማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች