አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ወደ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ገብተው መማር እንደሚፈልጉ ተማሪዎች ገለጹ፡፡

88

ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ተቀብለው በማስተማር ላይ ናቸው፡፡

በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ተማሪዎቻቸውን እስካሁን ገና አልተቀበሉም፡፡

ዩኒቨርሲቲዎቹ ሙሉ ዝግጅት አድርገው ተማሪዎቹን ለመጥራት የሰላሙን መረጋገጥ ብቻ እየጠበቁ እንደኾነም ነው እየገለጹ ያሉት፡፡

በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ተመልሰው ትምህርታቸውን መቀጠል እንደሚፈልጉ ነው የተናገሩት፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው ፊልሞን ግርማ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነው።

ወደሚማርበት ግቢ ተመልሶ ትምህርቱን ለመቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል፡፡ ተማሪ ፊልሞን በድህነት ያሳደጉትን ቤተሰቦቹን ተምሮ መርዳት እና ለሀገሩም አንዳች ፋይዳ ያለው ሥራ መሥራት እንደሚፈልግ ገልጾ ይህን ለማድረግ ግን ሰላም ወሳኝ ነው ብሏል፡፡

ሰላም ሲጠፋ በድህነት ተምረው ወላጅ እና ሀገርን መጥቀም የሚችሉ ተማሪዎች ሕልማቸውን ለማሳካት እንደሚቸገሩ ነው የሚገልጸው፡፡ ተማሪ ፊልሞን በውይይት የሚያምን እና ለወገኖቹ የሚያስብ ትውልድ መፍጠር እንደሚገባ ገልጾ ሁሉም ሰላማዊ አካባቢን ለመፍጠር እንዲተባበር ጠይቋል፡፡

የጎንደር ተወላጅ እንደኾነች የነገረችን የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሐይማኖት ግርማ ዩኒቨርሲቲዋ ይጠራል ብላ እየተጠባበቀች እንደምትገኝ ነው የተናገረችው፡፡

አሁን ላይ በአማራ ክልል የሚስተዋለው የሰላም እጦት እንደሚያሳስባት ገልጻለች። አሁን ያለው የሰላም እጦት ችግሮችን ተነጋግሮ እና ተደማምጦ የመፍታት ሰፊ ልምድ ባለው የአማራ ሕዝብ ይፈታል ብላ እንደምታምን ተናግራለች፡፡

ተማሪ ሐይማኖት በአማራ ክልል ያለው የሰላም ችግር በአጭር ጊዜ ተፈትቶ፣ ዩኒቨርሲቲዋም ጠርቷት ትምህርቷን የመቀጠል ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች።

ከኦሮምያ ክልል ወደ አማራ ክልል ተመድቦ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ እንደኾነ የነገረን ተማሪ ገመቹ በዳዳ “የአማራ ሕዝብ ፍቅር የኾነ ሕዝብ ነው፤ አሁን ያለው ኹኔታ ለዚህ ሕዝብ የሚገባ አይደለም” ሲል ገልጿል፡፡

ተማሪ ገመቹ ሕዝቡ በመነጋገር የሚያምን፣ ኩሩ፣ እና አስተዋይ መኾኑን በአካል አይቸዋለሁ፤ አሁን እየደረሰበት ያለው ችግር ተፈትቶ እኛም ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብተን ለመማር ይቻለን ዘንድ ለሰላሙ መሠራት አለበት ብሏል፡፡

“ሁሉም ሰው ለሰላም ዘብ ከቆመ የማይፈታ ችግር የለም” ሲልም ተማሪው ገልጿል። ተረጋግቶ ለመማር ሰላም ወሳኝ በመኾኑ ወደ ሰላም እና መነጋገር መመለስ ያስፈልጋል ነው ያለው፡፡ ሰላም ሰፍኖ፣ የሚወደው ሕዝብም ከችግሪ ተላቅቆ ዩኒቨርሲቲው ጥሪ አድርጎለት ወደ ባሕር ዳር እንደሚያቀና ያለውን ተስፋም ገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገራዊ ምክክሩ አካታችና የሀገራችንን ፈውስ የሚያረጋግጥ እንዲኾን ሁላችንም ጥረት ማድረግ አለብን” አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
Next article“60 ሚሊዮን ብር መድበን የምግብ ሸቀጥና እህል ለማቅረብ እየሠራን ነው” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር