“ሀገራዊ ምክክሩ አካታችና የሀገራችንን ፈውስ የሚያረጋግጥ እንዲኾን ሁላችንም ጥረት ማድረግ አለብን” አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

54

ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ሀገራዊ ምክክሩ አካታችና የሀገራችንን ፈውስ የሚያረጋግጥ እንዲኾን ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ማድረግ አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 3ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያቀረበውን የ2016 በጀት ዓመት የአራት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለልዩነቶቻችን ምክንያት በኾኑ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንዲሠራ ኃላፊነት መሰጠቱን አስገንዝበዋል። አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ሀገራዊ ምክክሩ ካለው የሕዝብ ብዛት አኳያ ጥራት ያለውና አካታችነቱ የተረጋገጠ መኾን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ዋና ኮሚሽነሩ ኘሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ተግባራቶቹን በአራት ምዕራፎች ከፍሎ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራቶቹን ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል::

በሂደቱም በአራት ወራት አፈጻጸሙ በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያና ኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ ተቋማትን ጨምሮ ተባባሪ አካላት በመለየት ሥልጠና ተሰጥቷል ነው ያሉት።

ከወረዳ እስከ ፌደራል ድረስ ያለውን የምክክር ተሳታፊዎች ልየታ አካታችና አሳታፊ በማድረግ ሂደት ከኮሚሽኑ ጋር አብረው የሚሠሩ መኾናቸውንም አስረድተዋል።

የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው በመጠናቀቅ ላይ መኾኑን የገለጹት ፕሮፌሰር መስፍን የአጀንዳ መረጣ ሥራው እንደተጠናቀቀ ወደ ተግባር ምዕራፍ የሚገባ መኮኑን እና ሕዝቡ በከፍተኛ ናፍቆት የሚጠብቀው ተግባር መኾኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

የተሳታፊዎችን ልየታ ሥራ በተቀመጠው ፕሮግራም መሰረት ለማከናወን ወቅታዊው የጸጥታ ችግር እና የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪዎች ምደባ ላይ ግልጽ አቅጣጫ አለመቀመጥ እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቁመዋል። ዋና ኮሚሽነሩ በክልሎች ያለውን የተሳታፊዎች መረጣና የአጀንዳ ልየታ በማጠናቀቅ አሳታፊና አካታች ሀገራዊ ምክክር ማስጀመር የቀጣይ ትኩረት አቅጫዎች መኾናቸውንም እንዳስረዱ ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተወካዮችን የመመልመል ሥራ ያልተከናወነባቸው ክልሎች ላይ በቀጣይ ወደ ሥራ ለመግባት እየተመቻቸ ነው” የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
Next articleአስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ወደ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ገብተው መማር እንደሚፈልጉ ተማሪዎች ገለጹ፡፡