
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ2016 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን የአራት ወር ተግባራት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአራት ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ኮሚሽኑ ከቅድመ ዝግጅት እስከ ትግበራ እና ክትትል በሚሉ ምዕራፎች ሥራዎችን ከፋፍሎ መሥራት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በዝግጅት ምዕራፍ ወደ ክልሎችና ከተማ አሥተዳደሮች እንዲሁም ወደ ወረዳ በመሄድ ባለድርሻ አካላትን በማግኘት የመለየት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡
በየደረጃው ተገምግሞ ጸድቆ ወደ ሥራ የገባው የምክክር ሂደቱ የትግበራ ሂደት መኖሩን ጠቅሰው፤ በየጊዜው አካሄዶቹ እየተፈተሹ እንደኾነ ገልጸዋል።
ተወካዮችን የመመልመል ሥራ ከአማራ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች ውጪ መካሄዱንም አስረድተዋል።
“ተወካዮችን የመመልመል ሥራ ያልተከናወነባቸው ክልሎች ላይ በቀጣይ ወደ ሥራ ለመግባት እየተመቻቸ ነው” ብለዋል ኮምሽነሩ።
የሀገራዊ ምክክር ሂደት በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ በሀገሪቱ ያለው አለመረጋጋት ትልቅ ፈተና መኾኑን አንስተው በመላ ሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መኾኑም ተመላክቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ሰብሰባ ቃለ ጉባኤን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
ዘጋቢ፡- አየለ መስፍን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!