
አዲስ አበባ: ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ-ቴሌኮም ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር የአጋርነት ስምምነት ውል ተፈራርሟል። ስምምነቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እና የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ ተፈራርመዋል። ይህ ስምምነት ለውጤታማ የውኃ እና የኢነርጂ አሥተዳደር ዲጂታል መፍትሔ መስጠትን ታሳቢ ያደረገ መኾኖ ተገልጿል።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢነጅር ሀብታሙ ኢተፋ ስምምነቱ መሥራያ ቤታቸው የሚፈልገውን ሥራ በሚገባ ለመፈጸም የሚያሥችል ነው ብለዋል። በውኃ ሃብት አሥተዳደር ዘርፍ ያለውን አቅም እና ጉልበት ለማሣደግ እና ለመጠቀም አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነውም ብለዋል።
ጎርፍ፣ ድርቅ እና የመሳሰሉ የተፈጥሮ አዳጋዎች በሚገጥሙ ጊዜ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ እና መፍትሔ ለመሥጠትም ያግዛል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚያደርገው ጥረት ከተቋማት ጋር በትብብር መሥራት አሥፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂን መጠቀም እና ማሣደግ የቅንጦት አይደለም፤ ሃብትን በሚገባ ለማሥተዳደር በዚህ ጊዜ የግድ አሥፈላጊ ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል አቅምን በማሳደግ የሀገር ሃብትን በሚገባ ለመጠቀም የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ።
ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት በሚገባ ለመወጣትም የቴክኖሎጂ አቅምን በሚገባ መጠቀም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡- ባዘዘው መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!